ቀጥታ፡

በዞኑ ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ስራ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል

ግራዋ ፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ስራ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱ ተገለጸ።

በዞኑ የዘንድሮ በጋ ተፋሰስ ልማት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የዞን ደረጃ በግራዋ ወረዳ በሜይራ ጉዲና  መንደር ተጀምሯል።


 

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሀመድ፤ በዞኑ ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ስራ አካባቢን ከመጠበቅ ባለፈ ለምርታማነት ማደግ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።


 

በተለይም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንጻር የተፋሰስ ልማት ስራ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።

የኦሮሚያ ክልል መሬት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መሰርት አሰፋ በበኩላቸው፤ የሐረርጌ  አርሶ አደሮች በተፋሰስ ልማት ባገኙት ውጤት አካባቢያቸውን መቀየር መቻላቸውን አንስተዋል።


 

በዞኑ ተጎሳቅሎ የነበሩ አካባቢዎችን መልክአ ምድር በመጠበቅና የአፈር ለምነትን በማሻሻል አረንጓዴ መላበሱን ገልጸው ይህም የተፋሰስ ልማት ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

የግራዋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብዲሻ ጃፈር የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ከሰባት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የሚከናወን መሆኑን ገልፀዋል።


 

በተፋሰስ ልማቱ ላይ የተሳተፉ አርሶ አደሮች ባለፉት አመታት በሰሩት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ በርካታ ጥቅም እንዳስገኘላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም