በአጎራባች አካባቢዎች ያለውን ሰላም በጋራ በመጠበቅ ልማት እንዲፋጠን እንሰራለን - ኢዜአ አማርኛ
በአጎራባች አካባቢዎች ያለውን ሰላም በጋራ በመጠበቅ ልማት እንዲፋጠን እንሰራለን
ነቀምቴ ፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦ በአጎራባች አካባቢዎች ያለውን ሰላም በጋራ በመጠበቅ ልማት እንዲፋጠን እንሰራለን ሲሉ የኦሮሚያ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አመራሮች ገለጹ።
የኦሮሚያ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የጋራ ሰላምና ልማት፣ የግጭት አፈታትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት በነቀምቴ ከተማ ተካሄዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙ የክልሎቹ ተወካዮች በአጎራባች አካባቢዎች ያለውን ሰላም በጋራ በመጠበቅ ልማትን ለማፋጠን እንደሚተጉ ገልጸዋል።
የኦሮሚያ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የጋራ ሰላምና ልማት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዲንሳ በየነ፣ ጽህፈት ቤቱ በአጎራባች አካባቢዎች ሰላምና ልማት እንዲጠናከር የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በክልሎቹ የጋራ ጥረት በተወሰዱ እርምጃዎችም አካባቢው ሰላም የሰፈነበት እና የልማት ስራዎች ያለመቋረጥ የሚካሄዱበት መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ህዝቡ ትኩረቱን በሙሉ ልማት ላይ ማድረግ እንዲችል እና የተፈጥሮ ሀብቱን ተጠቅሞ መለወጥ እንዲችል የአካባቢው አመራሮች የድርሻቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ይህ የወንድማማችነት መድረክ በነቀምቴ ከተማ ላይ ሲዘጋጅ ከውይይት በዘለለ በአካባቢው ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት ያስችላል ሲሉም አክለዋል።
ኦሮሚያ ክልል ፀጥታ እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ፣ የፀጥታ አካላት ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን በሰሩት የተቀናጀ ስራ በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል።
ክልሎቹም ተቀናጅተው ልማት እና ሰላምን ለማስቀጠል የጀመሩት ጥረት የበለጠ የሚጠናከር መሆኑንም አስረድተዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላምና ፀጥታ ምክትል ኃላፊ አቶ ኢሳም የሱፍ በበኩላቸው፤ ተቀራርቦ መስራት በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ያግዛል ብለዋል።
በተለይም የሰላም መንገዶችን አሟጦ ከመጠቀም ጎን ለጎን ችግሮች ሲያጋጥሙ የህግ ማስከበር ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ መፈጸም እንደሚገባም ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የሁለቱ ክልሎች የዞኖችና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም የጸጥታ አካላት አመራሮች ተሳትፈዋል።