ቀጥታ፡

በክልሉ ዘመናዊ የንብ ማነብ ስራን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው

አምቦ፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ዘመናዊ የንብ ማነብ ስራን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

''ምእራብ ሸዋን የማር ምርት ማእከል እናደርጋለን'' በሚል መሪ ሀሳብ ለሁለት ቀናት የሚቆይ የማር ምርት ኤግዚቢሽን እና ባዛር በአምቦ ከተማ ተከፍቷል።


 

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቶሌራ ደበላ፤ በክልሉ የተጀመረው የማር ምርት ኢኒሼቲቭ በውጤታማነት መቀጠሉን ገልጸዋል።

በክልሉ ዘመናዊ የንብ ቀፎን በማስፋፋት ምርታማነትን በማሳደግ የአልሚዎች ተጠቃሚነት እውን እንዲሆን ትኩረት መደረጉን አንስተው በተለይም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።


 

በዚህም ከአምስት አመት በፊት በክልሉ ይገኝ የነበረው 45 ሺህ ቶን የማር ምርት በ2017 ዓ.ም ወደ 69 ሺህ ቶን ማደጉን አንስተው የዘርፉ ልማት በየአመቱ ከፍተኛ ለውጥ እየመጣበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የምእራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ፤ በዞኑ በሌማት ትሩፋት መርኃ ግብር ጥሩ ውጤት ከተገኘባቸው ምርቶች አንዱ ማር መሆኑን አንስተው ይበልጥ ለማሳደግ በተለይም ዘመናዊ ቀፎዎችን የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የኤግዚቢሽኑ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፥ በዘርፉ ልማት መንግስት በሰጠው ትኩረትና በሚደረገው ድጋፍ ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን ገልጸዋል።

የዳኖ ወረዳ ነዋሪው አቶ ግርማ አለማየሁ ከአንድ ዘመናዊ ቀፎ 20 ኪሎ ግራም፣ ከሽግግር ቀፎ ከ10 እስከ 15 ኪሎ ግራም፣ ከባህላዊ ቀፎ ደግሞ ከአምስት እስከ 10 ኪሎ ግራም ማር እንደሚያገኙ አመልክተዋል።

ከሌሎች ግብርና ስራዎች ሌላ በማር ሽያጭ አመታዊ ገቢያቸውን በእጥፍ ማሳደጋቸውን ተናግረዋል፡፡


 

የቶኬ ኩታዬ ወረዳ ንብ አንቢ ፈይሳ ኩመላ፣ በንብ ማነብ ስራ ከተሰማሩ ሁለት አመት ወዲህ 25 ዘመናዊ፣ የሽግግርና ባህላዊ ቀፎ ተጠቅመው ያመረቱትን ማር በመሸጥ ገቢያቸውን ማሳደጋቸውንም ገልጸዋል።


 

በኤግዚቢሽኑ ላይ የክልልና የዞን የስራ ሀላፊዎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም ማር አምራቾችና ነጋዴዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም