ኢትዮጵያ ከውሃ ሀብቷ የኤሌክትሪክ ሀይል በማመንጨት ቀጣናውን በኃይል ለማስተሳሰር የጀመረችው ውጥን የሚበረታታ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከውሃ ሀብቷ የኤሌክትሪክ ሀይል በማመንጨት ቀጣናውን በኃይል ለማስተሳሰር የጀመረችው ውጥን የሚበረታታ ነው
ወላይታ ሶዶ፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከውሃ ሀብቷ የኤሌክትሪክ ሀይል በማመንጨት ቀጣናውን በኃይል ለማስተሳሰር የጀመረችው ውጥን የሚበረታታ መሆኑን 14ኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጉባኤ ተሳታፊዎች ተናገሩ።
14ኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንና የባለድርሻ አካላት የጋራ ጉባኤ ተሳታፊዎች የጊቤ-3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያን ዛሬ ጎብኝተዋል።
ተሳታፊዎቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ተጠቅማ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ቀጣናውን በኃይል ለማስተሳሰር የጀመረችው ውጥን የሚበረታታ ነው።
ከተሳታፊዎች መካከል የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ ዮሴፍ አካሉ፤ ኢትዮጵያ ከውሃ ሀብቷ ኃይል በማመንጨት ቀጣናውን ለማስተሳሰር የጀመረችው ውጥን መጠናከር ያለበት ነው ብለዋል።
የዚህ ማሳያ የሆነው የጊቤ-3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ መንግስት በዘርፉ እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
ዛሬ ግድቡን መጎብኘታቸው በሀገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ የሚያደርግ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ምክትልና የፊሲካል ፖሊሲ ሲቪልና ትብብር ዘርፍ ኃላፊ አቶ በለጠ ሙንኤ በበኩላቸው፤የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫው ኢትዮጵያ የውሃ ኃብቷን መጠቀም የሚያስችላትን አቅም ፈጥሯል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ለኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተደራሽነት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለሀገር ገጽታ ግንባታ እና ለአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
መንግስት የውሃ ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀም የያዘው ስትራቴጂ ተጠናክሮ ከቀጠለ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ይበልጥ ለማሳደግ ሰፊ ዕድል እንዳለም አንስተዋል።
ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት ከ500 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል ያሉት የሃይል ማመንጫ ጣቢያው ኦፕሬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ደጀኔ ጉታ ናቸው።
ግድቡ በአስር ተርባይኖች 1ሺህ 870 ሜጋ ዋት ኃይል በማመንጨት ከሕዳሴው ግድብ ቀጥሎ 2ኛው ትልቅ የኃይል ማመንጫ ሀገራዊ ፕሮጀክት መሆኑንም አስረድተዋል።
ኤሌክትሪክ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት አንገብጋቢ ጉዳይ በመሆኑ መንግስት የኃይል አቅርቦትን በማሻሻል የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት መስጠቱንም ተናግረዋል።
የጊቤ-3 ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ኃይል መጠን 18 ነጥብ 2 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ ግድቡን ከመጠበቅ ባለፈ በደለል እንዳይሞላ ለአረንጓዴ ልማት ትኩረት እንዲሰጥ አስገንዝበዋል።
የጋራ ጉባኤው በወላይታ ሶዶ ከተማ የተካሄደው "የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ትብብርና ቅንጅት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሃሳብ ነው።