በክልሉ ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬት በበጋ መስኖ ልማት በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬት በበጋ መስኖ ልማት በዘር ተሸፍኗል
በደሌ፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በእስካሁኑ እንቅስቃሴ ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬት በበጋ መስኖ በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ እና ሌሎች የክልል እና የዞን የስራ ሃላፊዎች በቡኖ በደሌ ዞን ዳቦ ሐና ወረዳ ዲዴሳ ቀበሌ በመስኖ እየለማ የሚገኘውን ስንዴ ጎብኝተዋል።
የቢሮው ሃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች በክልሉ በመስኩ ያለውን አቅም መለየት፣ ማወቅና መጠቀም ተችሏል።
በተለይም በክልሉ እየተተገበረ የሚገኘው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባለፈ የጊዜ አጠቃቀምን እንዲሁም የስራ ባህል በእጅጉ እየቀየረ፣ ለሀገርም እየጠቀመ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ የበጋ መስኖ ስራው አርሶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቅቆ ዓመቱን ሙሉ ማምረት እንዲችልም እድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል።
በተያዘው በጋ ወራትም በክልል ደረጃ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ለማልማት ታቅዶ በእስካሁኑ እንቅስቃሴ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አስታውቀዋል።
የበጋ መስኖ ልማቱን ስኬታማ ለማድረግም ከ50 ሺህ በላይ የውኃ መሳቢያ ሞተሮችን ለአርሶ አደሮች ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።
በቡኖ በደሌ ዞን በዘንድሮው የበጋ ወቅት 184 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ስንዴን ለማልማት ታቅዶ እስካሁን 149 ሺህ ሔክታር ያህሉ በዘር መሸፈኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሚን ደኑ ናቸው።
በዞኑ ከሁለት ዓመታት በፊት አርሶ አደሩ በክረምት ወቅት ብቻ በማምረት የበጋውን ወቅት ያለስራ ያሳልፍ እንደነበር አስታውሰው የበጋ ስንዴ ልማት መጀመሩ የስራ ባህል ከመቀየር ባለፈ ተጠቃሚነትን አሳድጓል ብለዋል።
በቡኖ በደሌ ዞን ዳቦ ሐና ወረዳ የዲዴሳ ቀበሌ አርሶ አደሮች ፣ ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ባለሙት የበጋ መስኖ ስንዴ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመትም በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ ለመሆን የግብርና ግብዓቶችን በአግባቡ ተጠቅመው ልማቱን እያካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።