ቀጥታ፡

የውጭ ሃገራት ፍልሰት በህጋዊ ሥርዓት እንዲመራ የተሰራው ሥራ ውጤት እያመጣ ነው 

ሆሳዕና፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦የዜጎችን ሰብአዊ መብትና ክብርን ለማስጠበቅ የውጭ ሃገራት ፍልሰት በህጋዊ ሥርዓት እንዲመራ የተሰራው ሥራ ውጤት እያመጣ መሆኑን የፍትህ ሚኒስቴር ገለፀ።

በሰው የመነገድ ወንጀልን በመከላከልና በዳያስፖራ ተሳትፎ ላይ የሚመክር የከፍተኛ አመራሮች መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።

በዚህ ወቅት የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ እንዳሉት፤ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ተለያዩ ሃገራት በፍልሰት የሚሄዱ ዜጎች ሰብአዊ መብታቸውና ክብራቸው ተነክቶ ለእንግልት እና ለሞት እየተዳረጉ ነው።


 

ችግሩን ለመከላከልና ለመቀነስ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ አዋጆችን ከመተግበር ባለፈ በሀገሪቱ በአዲስ መልክ ብሔራዊ ምክር ቤት እና የትብብር ጥምረት ጽህፈት ቤት ተቋቁሞ በቅንጅት በተሰራው ሥራ ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የሥራ ዕድሎችን በማስፋት የዜጎች ፍልሰት ጫናን ለመቀነስ መቻሉን አውስተዋል። 

ከስደት ተመላሽ ዜጎችን የማቋቋም ሥራ ትኩረት እንደተሰጠው በመጠቆም ወንጀል ፈጽመው በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ ዜጎች ከሚገኙበት ሀገራት ጋር በመቀናጀት ተጠያቂ የማድረግ ሥራም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍፁም አረጋ፤ በርካታ ዜጎች በህገ ወጥ ደላሎች ተታለው ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከዚያም ባለፈ ለህልፈት እየተዳረጉ መሆናቸውን ገልጸው፣ እነዚህን ዜጎች ለመታደግ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።


 

ለስደት ገፊ ምክንያቶችን በመለየት በሃገር ውስጥ እና በተለያዩ ሃገራት በህጋዊ መንገድ የሥራ ባለቤት እንዲሆኑ እየተሰራ ያለውን ሥራም በማሳያነት ጠቅሰዋል።  

ከተለያዩ ሀገራት ጋር የጋራ ቅንጅት በመፍጠር የህገ ወጥ ስደት አሳሳቢነት ከማስገንዘብ ባለፈ በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ወደ ሃገር ውስጥ የመመለስ ሥራም ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የዳያስፖራው ተሳትፎ እያደገ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

በህጋዊ መንገድ የሚላክን ገንዘብ ለማሳደግ በተሰራው ሥራም በተያዘው በጀት ዓመት ግማሽ ዓመት ህጋዊ የገንዘብ ዝውውሩ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተናግረዋል። 

በርካታ ዳያስፖራዎች በሀገር ውስጥ በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሳተፉ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም መዋዕለንዋያቸውን በማፍሰስ ለዜጎችም የሥራ ዕድል እየፈጠሩ መሆኑን አስረድተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በበኩላቸው፤ በክልሉ በሰው የመነገድ ወንጀል የሚሳተፉ ዜጎችን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው።


 

በተለያየ ምክንያት ተታለው በህገ ወጥ መንገድ ወደውጭ ሀገር የሚሄዱትን ከመከላከል ባለፈ ዜጎች ለሥራ ወደውጭ ሲሄዱ ህጋዊ አሰራርን እንዲከተሉ የማስገንዘብ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል ።

እንደእሳቸው ገለጻ፤ ከህገወጥ ፍልሰት ጋር በተያያዘ የሚታየውን ችግር ለመቀነስ ማህበረሰቡን ያሳተፈ ሥራ  እየተሰራ ነው።

ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ የፌደራልና የክልሉ የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣  የሃይማኖት አባቶች፣ የስደት ተመላሾችና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በመሳተፍ ላይ ናቸው። 

በተጨማሪም በደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ዚምባብዌና ታንዛንያ የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች በቨርችዋል እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም