ቀጥታ፡

የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ ዘርፉን በኢኖቬሽን የመደገፍ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ቢሾፍቱ፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦ የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ  ዘርፉን  በኢኖቬሽን የመደገፍ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ገለፁ። 

ሀገር አቀፍ የጤና አገልግሎት ጥራት እና ኢኖቬሽን ጉባኤ በኦሮሚያ ጤና ቢሮ አዘጋጅነት በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

የጤና  ሚኒስትር  ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ በመድረኩ እንደተናገሩት፤ የጤና አገልግሎት ጥራትን በማሻሻል ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል ላይ ትኩረት ተሰጥቷል።

የጤና አገልግሎት ጥራቱን  ለማሻሻል ኢኖቬሽንና ዲጂታላይዜሽን ላይ በስፋት በመስራት ፍትሃዊ ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ  እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ኃላፊ ፕሮፌሰር ነጻነት ወርቅነህ በበኩላቸው፤ በክልሉ የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል  ለዲጂታላይዜሽን፣ ለሰው ሃይል  አቅም ግንባታና የሕክምና ግብአት ማሟላት ላይ በሰፊው መሰራቱን አንስተዋል።


 

የጤና አገልግሎት ጥራት ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍና አዳዲስ ፈጠራዎችን  ወደ ስራ በማስገባት  የተገልጋዩን እርካታ እውን ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በጤና አገልግሎት ጥራት ፍትሃዊነትና ተደራሽነት ላይ የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል  የጤና ኢኖቬሽን  ስራዎችን  ባህል ማድረግና   ትብብሩን ማጠናከር  እንደሚገባም  ተናግረዋል።  

የጤናው ዘርፍ የኢኖቬሽን ስራዎችን የሚያሳዩ ኤግዚቢሽኖች፣ ጥናትና ምርምሮች እንዲሁም ትብብርን የሚያጠናክሩ ውይይቶችና ሌሎች ሁነቶች በጉባኤው ይካሄዳሉ ብለዋል።  

በጉባኤው ላይ የፌዴራልና የክልል አመራሮች፣ የዓለም ጤና ድርጅትና ዩኒሴፍ ተወካዮች፣ የምርምር ተቋማት፣ የግሉ ሴክተር እና ግብረሰናይ ድርጅቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም