የሃይማኖት አባቶች የክልሉን ሰላም ለማጽናት ሊተጉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት አባቶች የክልሉን ሰላም ለማጽናት ሊተጉ ይገባል
ጋምቤላ ፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦የሃይማኖት አባቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተደማጭነት በመጠቀም የክልሉን ሰላም ለማጽናት ሊተጉ እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።
በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሃይማኖት አባቶች ጋር የውይይት መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድሯ በመድረኩ ላይ እንዳሉት የሃይማኖት አባቶች ሰላምን በመገንባት ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው።
መንግስት በክልሉ በሚያከናውናቸው የሰላም ግንባታ ስራዎች ላይ የሃይማኖት አባቶች አስተዋጽኦ የላቀ በመሆኑ መድረኩ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ የአመለካከት፣ የአስተሳሰብና የነጠላ ትርክትን በመግራት በኩል የሃይማኖት አባቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተሰሚነት ተጠቅመው ለክልሉ ሰላም ሊተጉ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በክልሉ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና የህዝቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የሰላም ግንባታ ስራዎቻችንን አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሯ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በክልሉ የተገኘውን ሰላም ይበልጥ ለማጽናት በሚደረገው ጥረት የሃይማኖት አባቶች እገዛ ሊጠናከር ይገባል።
በተለይም የሃይማኖት አባቶች የጋራ የሆኑ እሴቶችን በማስተማር ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት የበኩላቸውን አበርክቶ እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
በመከላከያ ሰራዊት የዳሎል ማዕከላዊ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀነራል ሙላቱ ጀልዱ በበኩላቸው ፤ትውልድን በስነ-ምግባር በማነጽ ረገድ የሃይማኖት ተቋማት የጎላ ሚና አላቸው ብለዋል።
በመሆኑም የእምነት አባቶች ህዝቡን ስለ ሰላም በማስተማር የክልሉን ሰላም ይበልጥ ለማጽናት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የውይይት መድረኩ ተሳታፊ የሃይማኖት አባቶች የክልሉን ሰላም ለማጽናት ከመንግስት ጎን በመሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በተለይም በየእምነት ተቋማቱ ማህበረሰቡን በመልካም ስነ-ምግባር በማነጽና ሰላምን በማስፈን ረገድ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል።