ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዜጎች ተሳትፎ እንዲጠናከር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የላቀ ሚናቸውን ለመወጣት እየተዘጋጁ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዜጎች ተሳትፎ እንዲጠናከር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የላቀ ሚናቸውን ለመወጣት እየተዘጋጁ ነው
ወላይታ ሶዶ፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦ በግንቦት ወር ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዜጎች ተሳትፎ እንዲጠናከር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የላቀ ሚናቸውን ለመወጣት እየተዘጋጁ መሆኑን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ምርጫው ሂደት ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።
ለምርጫው ሂደት የቦርዱ የተሟላ ዝግጅት እንዳለ ሆኖ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራትና አጠቃላይ የዜጎች ጠንካራ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።
በዚህም መሰረት የዜጎች የምርጫ ተሳትፎ እንዲጠናከር በማድረግ በኩል በተለይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዝግጁነት ምን ይመስላል ሲል ኢዜአ የሚለከታቸው አካላትን አነጋግሯል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ፤ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት ሁነኛ መሰረት በሆነው የምርጫ ሂደት የዜጎች ጠንካራ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህ ሂደትም ዜጎች በቂ ግንዛቤ አግኝተው በእውቀት ላይ ተመስርተው መብታቸውን መጠቀም እንዲችሉ ድርጅቶቹ የማስተማርና የማስገንዘብ ስራ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በዚሁ መሰረትም በመጪው ግንቦት ወር ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዜጎች ተሳትፎ እንዲጠናከር የሲቪክ ማህበራት የላቀ ሚናቸውን ለመወጣት እየተዘጋጁ መሆኑን አንስተዋል።
በባለስልጣኑ የታቀፉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ አጠቃላይ ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ54 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምርጫን የመታዘብ፣ እንዲሁም ህብረተሰቡን ለማስተማር ፈቃድ በመስጠቱ ምህዳሩን አስፍቶልናል ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ታደሉ እጀታ ናቸው።
ለምርጫው ሰላማዊ ሂደት ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀቱን በመግለጽ።
ለምርጫ ሂደት መሳካት የዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በማንሳት በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው እንዲሳተፉ ድርጅቱ ሚናውን ይወጣል ሲሉም አክለዋል።
የሲዳማ ክልል ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ማስረሻ ክብረት፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በምርጫ ሂደት አወንታዊ አበርክቶ እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት የሲቪክ ማህበራት ሚናቸውን መወጣት የሚያስችል ዝግጁነት እንዳላቸውም ነው ጨምረው የተናገሩት።
በአንድ ሀገር የምርጫ ሂደት ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሲቪክ ማህበራት ሚና የላቀ መሆኑ ይታመናል።