ባህላዊ እሴቶች የወል እውነቶችና የብሔራዊ ትርክቶች መሠረት ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ባህላዊ እሴቶች የወል እውነቶችና የብሔራዊ ትርክቶች መሠረት ናቸው
ሚዛን አማን፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦ ባህላዊ እሴቶች የወል እውነቶችና የብሔራዊ ትርክቶች መሠረት በመሆናቸው ለሀገር ግንባታ ያላቸውን ሚና ለማጉላት እየተሰራ ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።
የቤንች ዘመን መለወጫ በዓል "ቢስት ባር" በሚዛን አማን ከተማ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።
በበዓሉ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር እንዳሉት ኢትዮጵያ የብዝኃ ባህሎች ማዕከልና የመቻቻል ማሳያ የሆነች ታላቅ ሀገር ናት።
ለከፋፋይና ነጣጣይ ትርክት የማይመቹ ሕዝቦች መገኛ በመሆኗ በሁሉም አካባቢዎች በባህላዊ በዓላትና ሌሎች ኩነቶች አብሮነታችን ደምቆ መታየቱን እንደቀጠለ ነው ሲሉም አክለዋል።
የብሔረሰቦች ባህላዊ እሴቶች ደግሞ የወል እውነቶችና የብሔራዊ ትርክቶች መሠረት በመሆናቸው ለሀገር ግንባታ ያላቸው ሚና ጎልቶ እንዲወጣ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ያሉንን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ወደ ጥቅም በመቀየር ለኢትዮጵያ ብልጽግና መስፈንጠሪያ እንዲሆኑ ማስቻል ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።
ዛሬ የተከበረው የቤንች ዘመን መለወጫ "ቢስት ባር" በዓል የደረሰን እህል ተከፋፍሎ በመቃመስ ወደ አዲስ ዓመት የሚሸጋገሩበት እንዲሁም ክረምቱን በሰላም ስለተሸጋገረ ምስጋና የሚቀርብበት እንደሆነ ተናግረዋል።
የእርስ በርስ ግንኙነት የሚጠናከርበትና የይቅርታ በዓል በመሆኑ የጥላቻን ግድግዳ በማፍረስ ሰላም የማጽናት ዕሴቱ ከክልሉ አልፎ ለሀገር የሚጠቅም ነው ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) በክልሉ ለብሔረሰቦች ባህል ልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ያለ ልዩነት የሚከበረው የቢስት ባር ለክልሉ ህዝቦች አብሮነት መጠናከር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ይዘቱን ሳይቀይር ለትውልድ እንዲተላለፍ እንደሚሰራም አመልክተዋል።
በዓሉን በአብሮነት ስናከብር ድኅነትን ለማሸነፍ አቅም የምንፈጥርበት ጭምር መሆን አለበት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ለቱሪዝም ልማት የሚሰጠውን ትኩረት በማጠናከር የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱንም አመልክተዋል።
የቢስት ባር በዓል ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትርጉም ስላለው ያሉትን እሴቶች በማጎልበት ለትውልድ ለማስትላለፍ ይሠራል ያሉት ደግሞ የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሀብታሙ ካፍትን ናቸው።
ሌሎች ቱባ ባህሎችን ወደ አደባባይ በማውጣት የጥንታዊ አባቶቻችንን ጥበብና ፍልስፍና ለልማታችን ተደማሪ አቅም እንዲሆን በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ቡዛብ ደመላሽ እና ወጣት ሜሮን ሰይድ በዓሉ የማናውቃቸውን ጠቃሚ የቢስት ባር እሴቶችን እንድንረዳ አስችሎናል ነው ያሉት።
ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በአንድነት የሚከበር በዓል በመሆኑ ትውፊታዊ ይዘቱን ሳይለቅ እንዲቀጥል የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።