በጉጂ ዞን ለአምራችና አገልግሎት ሰጭ ኢንተርፕራይዞች ከ348 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በጉጂ ዞን ለአምራችና አገልግሎት ሰጭ ኢንተርፕራይዞች ከ348 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር ተፈጥሯል
አዶላ፤ ጥር 5/2018 (ኢዜአ)፡- በጉጂ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት ለኢንተርፕራይዞች ከ348 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር መመቻቸቱን የዞኑ የስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ገለጸ።
በጽህፈት ቤቱ የስራ እድል ፈጠራ ባለሙያ አቶ ቢራራ ገመዳ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት በግብርና፣ በጎጆ ኢንደስትሪ፣ በግንባታና በአገልግሎት መስክ ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ተመቻችቷል።
ኢንተርፕራይዞቹ የወተት፣ ስጋ፣ እንቁላል እንዲሁም የንብ ቆፎ፣ የቤትና የቢሮ እቃዎችንና ሌሎችንም በማምረት ለገበያ ማቅረባቸውን አመልክተዋል፡፡
የኢንተርፕራይዞችን ውጤታማነት ለማሳደግም ለ537 አምራችና አገልግሎት ሰጭ ኢንተርፕራይዞች የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል፡፡
ለኢንተርፕራይዞቹ ከ348 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፈጠሩን ጠቁመው የገበያ ትስስሩም ከማህበራት፣ ከመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ ከግብርና፣ ከጤናና ከሌሎችም የልማት ድርጅቶች ጋር የተፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል ።
በዞኑ አዶላ ከተማ የገበያ ትስስር ከተመቻቸላቸው ኢንተርፕራይዞች መካከል ቢሊሴ ቁምነገር የዘመናዊ ቀፎ ማምረቻ አንዱ ነው፡፡
የኢንተርፕራይዙ አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ መና በገበያ ትስስሩ ምርታቸውን በብዛትና በጥራት በማቅረብ ገቢያቸውን ማሳደግ እንደቻሉ ጠቁመዋል፡፡
መንግስት የፈጠረላቸውን የገበያ ትስስር በመጠቀም ዘመናዊ ቀፎዎችን በብዛት በማምረት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
እስካሁን ለአዶላ ከተማ አስተዳደር፣ ለግርጃ እና ለአናሶራ ወረዳ አስተዳደሮች 240 ዘመናዊ የንብ ቀፎ በተመጣጣኝ ዋጋ በማስረከብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ለመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤት ካቀረቡት ዘመናዊ ቀፎ ሽያጭ ከ360 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በኦዶላ ከተማ የገዱፋ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ደስታ ግርማ በበኩሏ ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቀች በኋላ ከአምስት ጓደኞቿ ጋር በመደራጀት መንግሥት ባመቻቸላቸው የመስሪያ ቦታና የብድር አገልግሎት የጣውላ መሰንጠቂያ ኢንተርፕራይዝ በመክፈት ወደ ስራ ገብተዋል።
ስራውን ለማሳደግም ከመንግስት የሙያ ማሻሻያና የሂሳብ አያያዝ ስልጠና በማግኘት ጠንክረው በመስራት ሀብት ለማፍራት እየተጉ መሆናቸውን ተናግራለች።
የገበያ ትስስር መፈጠሩ ምርትና አገልግሎትን በጥራት እና በብዛት በማምረት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው አስረድታለች።