ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ የቱሪዝም ሀብቶችን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ዝግጅት ተደርጓል

ጎንደር ፤  ጥር  5/2018(ኢዜአ)፡ - በጎንደር ከተማ የሚከበረውን የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ  የአካባቢውን  የቱሪዝም ሀብቶችንና የኢንቨስትመንት ጸጋዎችን  ይበልጥ  ለማስተዋወቅ ዝግጅት መደረጉን  የከተማው  አስተዳደር  ገለፀ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው  በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤  የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱ ባሻገር  አብሮነትንና  ወንድማማችነትን  የማጠናከር  ፋይዳው የጎላ  ነው፡፡

በጎንደር  በሚከበረው በዚሁ በዓል ላይ  ለመታደም  የሚመጡ እንግዶችን በመቀበል  አይረሴ ቆይታ  እንዲያሳልፉ ማድረግ  የሚያስችል  ዝግጅት  መደረጉን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጓዳኝ በከተማዋ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦች ለጎብኝዎች ምቹ መደረጋቸውን የአጼ ፋሲል ቤተ መንግስት  እድሳትና ጥገና  በማሳያ ጠቅሰው አስረድተዋል፡፡


 

የቤተ መንግስቱ እድሳት ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተዳምሮ ለጥምቀት በዓል ልዩ ድምቀት እንደሚያጎናጽፈው ጠቁመዋል።

በዓሉን ለመታደም የሚመጡ ቱሪስቶች  የከተማውን የመስህብ ሀብቶች እና  የኢንቨስትመንት ጸጋዎች  በምሽት  ጭምር ይበልጥ በማስተዋወቅ የማስጎብኘትና  የኢንቨስትመንት ፎረም ዝግጅት መደረጉን  አንስተዋል።

በከተማው በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመሰማራት ለሚፈልጉ የሀገር ውስጥና የውጪ ባለሀብቶች እንዲሁም ዲያስፖራዎች ከ500 ሄክታር በላይ የኢንቨስትመንት  መሬት መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል፡፡

እስከ ጥምቀት ዋዜማ ባሉት ቀናት  የተለያዩ ሁነቶችና የባሕል ሳምንት ፌስቲቫል እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡


 

የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች  በዓሉ በስኬት እንዲከበር የድርሻቸውን ለመወጣት  ተደራጅተው መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፤ ከ2ሺ 800 በላይ ወጣቶችም በበጎ ፈቃድ  ስራ ላይ መሰማራታቸውን ገልጸዋል፡፡

የከተማው አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች እንግዶችን ለመቀበል የሚያስችላቸውን የተሟላ ዝግጅት ማድረጋቸውን አንስተዋል።  

አንድ እንግዳ ለአንድ አባወራ በሚል በእንግዳ ተቀባይነት ባሕል መሰረት ሕዝቡ መኖሪያ ቤቱን አዘጋጅቶ በዓሉን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ በመጠባበቅ ላይ አንደሚገኝ  ጠቁመዋል፡፡

በጎንደር ከተማ በሚከበረው የጥምቀት በዓልም 2 ሚሊየን እንግዶች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመልክቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም