ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከ8 ሺህ በላይ የሚሆኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ስራ እንዲገቡ ውሳኔ ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በግማሽ ዓመቱ ከ262 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ከ8 ሺህ በላይ የሚሆኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ስራ እንዲገቡ ውሳኔ ማግኘታቸውን የክልሉ ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ገለጸ።

በዘርፉ ለመሰማራት ጥያቄ ላቀረቡ አካላት የክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርድ የሰጠውን ውሳኔን አስመልክቶ የክልሉ ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አህመድ ኢድሪስ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በክልሉ ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንን ጨምሮ ከተሞችም ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያጠናክሩ የተደረገ ሲሆን፤ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አማካኝነትም የኢንቨስትመንት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ጥያቄ ላቀረቡ አካላት የክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርድ በሁለት ዙር ውሳኔ መስጠቱን ገልጸዋል።

የክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርድ በጥቅምት ወር ባካሄደው የመጀመሪያ ዙር ስብሰባ ከ90 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 3ሺህ 163 ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ውሳኔ እንዲያገኙ አድርጓል።

ፕሮጀክቶቹ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ህጋዊ ሂደቶችን አጠናቀው ስራ የጀመሩ ሲሆን በሙሉ አቅም ወደ ስራ ሲገቡ ከ200 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ቦርዱ በታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ ባካሄደው ስብሰባ 172 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 5ሺህ 158 ፕሮጀክቶች ፍቃድ እንዲሰጥ መወሰኑን ገልጸዋል።

እነዚህ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በ45 ቀናት ውስጥ ህጋዊ ሂደቶችን አጠናቀው ወደ ስራ እንዲገቡ እንደሚደረግ ገልጸው ፕሮጀክቶቹ በሙሉ አቅማቸው ስራ ሲጀምሩ ከ400ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ያስገኛሉ ብለዋል።

በአጠቃላይ በግማሽ ዓመቱ ከ262 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ከ8ሺህ በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፈቃድ ማግኘታቸውን አስረድተዋል።

ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ የተወሰነው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት፣ የሀገር ውስጥ ባለህብቶች፣ የተሻለ ሀብት ያፈሩ አርሶ አደሮች፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ተሰማርተው ሀብት ያፈሩ ወጣቶች እንዲሁም የህብረት ስራ ማህበራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ ፕሮጀክቶች ፈጥነው በሙሉ አቅም ወደ ስራ መግባት እንዲችሉ የመሬት እና ፋይናንስ አቅርቦት፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና የሰለጠነ የሰው ሃይል የማቅረብ ስራ በቢሮው አማካኝነት እንደሚከናወንም አስረድተዋል።

የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ በአማዛኙ ተኪ ምርቶች ላይ አተኩረው እንዲሰሩ እንደሚደረግ አመልክተው፤ ፍቃድ ከተሰጣቸው የኢንቨስትመንት ፕሮጀቶች መካከል 148 የሚሆኑት በቡና ዘርፍ የሚሰማሩ መሆናቸውንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም