በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው የአካባቢውን ስነምህዳር በመጠበቅ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው የአካባቢውን ስነምህዳር በመጠበቅ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል
አሶሳ፤ ጥር 5/2018 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሲከናወን የቆየው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የአካባቢውን ስነምህዳር በመጠበቅ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የዘንድሮው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደረጃ አሶሳ ዞን ቡልድግሉ ወረዳ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ሀሊፋ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የአካባቢውን ስነምህዳር በመጠበቅ ምርታማነት እንዲጨምር አድርጓል።
በተለይም የተፋሰስ ልማት ስራ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች የሚተከሉ ችግኞች አፈርና ውሃን ከመጠበቅ ባለፈ ለአርሶአደሩ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እያስገኙ ነው ብለዋል።
በዘንድሮው ዓመት ከ57 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለማከናወን እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ ጥቅሙን በመረዳት በየአካባቢው ተሳትፎውን እያሳደገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በክልሉ እየተከናወነ የሚገኘው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ኃላፊው አንስተዋል።
የቡልድግሉ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በክሪ አብዱላሂ በበኩላቸው፤ በወረዳው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መከናወን ከጀመረ ወዲህ የደን ሽፋን እያደገ እና የአካባቢው አየር ንብረት እየተስተካከለ መምጣቱን ተናግረዋል።
ወረዳው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አቅራቢያ በመገኘቱ የሚከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አክለዋል።
በመርሃግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።