ቀጥታ፡

የጥበብ ሥራዎች የማህበረሰብን መልካም ዕሴት በማጋመድ የወል ትርክት መገንቢያና የዘመናት አሻራ ማስታዎሻ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦ የጥበብ ሥራ ውጤቶች የማህበረሰብን መልካም ዕሴት በማጋመድ የወል ትርክት መገንቢያና የዘመናት አሻራ ማስታዎሻ መሆናቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዲን አገኘሁ አዳነ ገለጹ።

አቶ አገኘሁ አዳነ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ትምህርት ቤቱ ከተቋቋመበት ከ1950 አንስቶ አንቱታን ያተረፉ ብቁ ሙያተኞችን እያፈራ ይገኛል።

በመጀመሪያ ዲግሪ በአምስት ዘርፎች እንዲሁም በድህረ-ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞች ሥርዓተ-ትምህርት በመቅረጽ የመማር ማስተማር ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ከተቋሙ የሚመረቁ ተማሪዎችም የጥበብ ሥራ ማስታወሻ የማበርከት ባህል ዕድገት ትምህርት ቤቱ ከፍተኛ የሥነ-ጥበብ ክምችት ሥራዎች እንዲኖሩት ማስቻሉን ተናግረዋል።

የሥነ-ጥበብ ሥራ ክምችቶቹ ተማሪዎች ከቀደምቶቻቸው የሚማሩበትን ዕድል በመፍጠር የኢትዮጵያን ሥነ-ጥበብ ለሚያጠኑ ተመራማሪዎችና ማህበረሰባዊ የሥነ-ጥበብ ንቃተ ሕሊና እየፈጠረ ነው ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲውን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ በዓልን በማስመልከትም ትምህርት ቤቱ ማራኪ የሆኑ የጥበብ ሥራ ውጤቶችን ለህዝብ ዕይታ ክፍት ማድረጉን አስታውቀዋል።


 

የትምህርት ቤቱን የጥበብ ሥራ ውጤቶች መጎብኝት የሚፈልግ ሁሉ በሥራ ሰዓት ከሰኞ እስከ ዓርብ እና ቅዳሜ እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ መጎብኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

የሥነ-ጥበብ ሥራ ውጤቶች መልካም ዕሴትና ማህበራዊ ትስስር ማጠናከሪያ የወል ገመድ በመሆናቸው የመንግሥታትም ሆነ የዘመናት አሻራዎች ማስታዎሻ ናቸው ብለዋል።

በአዲስ አበባ እና በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ ምኅዳርን መፍጠር የሚያስችሉ ማራኪ የሥነ-ውበት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ይህም የኢትዮጵያን የሥነ-ጥበብ ፍሬዎች በአደባባይ በመግለጥ ዜጎች ለጠንካራ ሀገር ግንባታ የሚጠቀሙበትን ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በሀገር ውስጥና ዓለም መድረክ አንቱታን ያተረፉ ሙያተኞችን በማፍራት በሀገር ግንባታ የጥበብ ሥራ ገንቢ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅትም መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት መነሻ በማድረግ የትምህርት ቤቱ ምሩቃን በኢትዮጵያ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች የጥበብ አሻራቸውን በማኖር ገንቢ ሚና እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በትምህርት ቤቱ የዲዛይን ዲፓርትመንት ኃላፊ ዑስማን ሀሰን በበኩላቸው፤ የማህበረሰብን ሁለንተናዊ ዘይቤ የሚገልጡ የጥበብ ውጤቶች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲውን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ በዓልን በማስመልከትም ትምህርት ቤቱ ለህዝብ ዕይታ ክፍት ያደረጋቸውን ማራኪ የጥበብ ውጤቶች ማህበረሰቡ እንዲጎበኝ ጋብዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም