የኢትዮጵያን የንግድ ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ የማክሮ ኢኮኖሚ እና የሕግ ማሻሻያ ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የንግድ ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ የማክሮ ኢኮኖሚ እና የሕግ ማሻሻያ ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የንግድ ምህዳር ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ የማክሮ ኢኮኖሚ እና የሕግ ማሻሻያ መደረጉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮ - ጃፓን የንግድ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ በመልካም ጎዳና ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም በጃፓን ገበያ ለኢትዮጵያ ቡና፣ ለሰሊጥ ለአበባ እንዲሁም እሴት ለተጨመረባቸው እንደ ጨርቃጨርቅ እና የቆዳ ውጤቶች ያለው ፍላጎት እያደገ መምጣቱን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የንግድ ከባቢን ለማሻሻል፣ ተወዳዳሪነትን መጨመርና የግል ዘርፉን ማነቃቃት የሚያስችሉ አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ እና የሕግ ማሻሻያዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የጃፓን ባለሀብቶች በዚህ ሰፊ የገበያ ልዩ እድሎች እንዲጠቀሙም ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ፎረሙ የሁለቱ ሀገራት የንግድ መሪዎች ተጨባጭ አጋርነትንና የኢንቨስትመንት እድሎችን የሚያዩበት መሆኑን አመልክተዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ እስያ እና ፓስፊክ ሀገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ደዋኖ ከድር በበኩላቸው፤ ጃፓን ለኢትዮጵያ የልማት ጉዞ የቴክኒክ እውቀትና ልምድን በማካፈል ድጋፍ እያደረገች መሆኑን ጠቅሰዋል።
የጃፓን መንግስትና የግሉ ዘርፍ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት እያደረጉት ያለውን አስተዋፅኦ በማድነቅ የጃፓን አልሚዎችም እነዚህን ሰፊ እድሎች እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኩኒሚትሱ አያኖ(ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ማዕከልና ቀጣናዊ የኢንዱስትሪ መሠረት የመሆን አቅሟ በጃፓን ኩባንያዎች ዘንድ ትልቅ ትኩረት ማግኘቱን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የዘርፉን እድገት ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች የሚደነቁ መሆናቸውንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር)፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ ብቻ ሳይሆን ጥራት ያለው፣ ዘላቂና የስራ ዕድል የሚፈጥር እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያመጣ ኢንቨስትመንት እንዲኖር እንደምትፈልግ ተናግረዋል።
መንግስት በሀገሪቱ ለሚሰማሩ የውጭ ባለሃብቶች ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ እንደሚያቀርብ ጠቁመው፤ በዚህ ረገድ ፎረሙ የጃፓን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሳተፉ መንገድ እንደሚከፍት ገልጸዋል።