የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ያካተቱ የተሽከርካሪ ታርጋዎችን ሥራ ላይ ሊያውል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ያካተቱ የተሽከርካሪ ታርጋዎችን ሥራ ላይ ሊያውል ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አሁን እየተጠቀመበት ያለውን የተሽከርካሪ ታርጋ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ባካተተ አዲስ ታርጋ ሊቀይር መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል አስታወቁ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወር የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እንደተናገሩት ፖሊስ አሁን እየተጠቀመባቸው ያሉ የተሽከርካሪ ታርጋዎችን ሙሉ በሙሉ በመቀየር አዳዲስና ዘመናዊ ታርጋዎችን በቅርቡ ስራ ላይ ለማዋል ዝግጅት ማጠናቀቁን ተናግረዋል።
ይህም ተቋሙ የወንጀል መከላከልና ምርመራ ስራውን በዘመናዊ መንገድ ለመምራት ከጀመራቸው የሪፎርም ስራዎች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
አዲሱ ታርጋ የረቀቁ የቴክኖሎጂ ቁልፎች ያሉት ሲሆን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስን ብቻ የሚወክል፣ የተቋሙን የሙያ ብቃት እንዲሁም የዲሲፕሊን ደረጃ የሚያንፀባርቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽነር ጀነራሉ አዲሱ ታርጋ ታትሞ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በይፋ ጥቅም ላይ እንደሚውል አረጋግጠዋል።