ኢትዮጵያን በአቪዬሽን ዘርፍ ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል አቅም እየተገነባ ነው - ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን በአቪዬሽን ዘርፍ ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል አቅም እየተገነባ ነው - ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን በአቪዬሽን ዘርፍ ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል አቅም እየተገነባ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ለሁለት ተቋማት የስራ ፈቃድ ሰጥቷል።
የስራ ፈቃዱ የተሰጠው በአውሮፕላን ጥገና ዘርፍ በኢትዮጵያ አየር ሃይል ውስጥ ለተቋቋመው እና ለግል አየር መንገዶች ጥገና ለሚሰጠው ተቋም ነው።
ባለስልጣኑ በተመሳሳይ ለዓለም አቀፍ የካርጎ አቪዬሽን አገልግሎት ደግሞ የአቪዬሽን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የስራ ፈቃድ ሰጥቷል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያን የበረራ ትራንስፖርት (አቪዬሽን) ማዕከል ለማድረግ የተለያዩ የለውጥ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው፡፡
በዚህም በዘርፉ የኢትዮጵያን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ አቅም እየተገነባ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ግንባታውን በይፋ ያስጀመሩት የቢሾፍቱ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል፡።
በዛሬው ዕለትም ለሁለቱ ተቋማት የተሰጠው የስራ ፈቃድ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተዋል፡፡
ለኢትዮጵያ አየር ሃይል በጥገና ዘርፍ የተሰጠው የስራ ፈቃድ የግል አየር መንገዶች ለአውሮፕላን ጥገና የሚያወጡትን ወጪ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የዓለም አቀፍ ካርጎ አቪዬሽን አገልግሎት የአቪዬሽን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ፈቃድ ማግኘቱ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት በሚደረገው ሀገራዊ ጉዞ ትርጉም ያለው ሚና እንደሚኖረው አስታውቀዋል።
ማሰልጠኛው ከኢትዮጵያ አልፎ በአህጉር ደረጃ ባለሙያዎችን ለማፍራት ለሚደረገው እንቅስቃሴ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዮሃንስ አበራ በበኩላቸው፤ ለተቋማቱ እውቅና የተሰጠው አስፈላጊውን መስፈርት ማሟላታቸው ተረጋግጦ መሆኑን ተናግረዋል።
በስነ-ስርዓቱ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር)፣ የኢፌዴሪ የአየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡