ቀጥታ፡

የተቋሙ የዘመናዊነት ጅማሮና ዲጂታል ኢትዮጵያ ይዞት የመጣው ዕድል

ኢትዮጵያ ዘመናዊነት መላበስ በጀመረችበት ወቅት ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ ከተቋቋሙ ቀደምት ተቋማት መካከል አንዱ ነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፡፡

አገልግሎቱ አሰራሩን ሊያቀላጥፉ የሚችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምና የደንበኞችን እርካታ መጨመር ባለመቻሉ በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያስተናግድ ቆይቷል።

በለውጡ ዓመታት በኢትዮጵያ ዘመናዊ፣ ዘመን ተሻጋሪና ጠንካራ የመንግሥት የአገልግሎት ሥርዓት መዘርጋት የሚያስችል ሪፎርም መካሄዱ ይታወቃል።

የመንግስት አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ በማዘመን ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ከብልሹ አሰራር ለማጽዳት የተጀመረው ጥረት ሕብረተሰቡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ እርካታ እንዲኖረው እያደረገ ይገኛል።

ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ኤሌክትሪክ ወሳኝ እንደመሆኑ አገልግሎቱ ለዚህ አስቻይ ሁኔታን ሊፈጥሩ የሚችሉ አሰራሮችን መተግበር ግድ ይለዋል።

አገልግሎቱ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የኤሌክትሪክ ሽፋንን ለማሳደግ የጀመራቸው ሥራዎች ውጤታማ እየሆኑ ይገኛሉ።

ነገር ግን ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት የተያዘው ግብ እውን እንዲሆን ተቋሙን ማዘመን ወሳኝ ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አሁን ካለው ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር አሰራርን ከማዘመንና ቴክኖሎጂን ከመጠቀም ውጪ በቀደመው አሰራር ሀገርን ማሻገር አይቻልም ብለዋል።

ይህን ተከትሎ አገልግሎቱ አሰራሩን በቴክኖሎጂ የታገዘ ማድረግ፣ ልምድ ካላቸው ተቋማት ጋር በጋራ መስራት እንዲሁም የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ለቴክኖሎጂ ምቹ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የተያዙ ግቦች እውን እንዲሆኑ ከፍተኛ እገዛ እንዳለው ነው ያስረዱት።

ዋና ሥራ አሥፈጻሚው እንደሚሉት ተቋማቸው ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የደንበኞችን እርካታ የሚጨምሩ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል።

ለአብነት የደንበኞችን እንግልት ለመቀነስና ተገልጋዮች ባሉበት ሆነው የአገልግሎት ክፍያቸውን የሚፈጽሙበት አሰራር ተግባራዊ ማድረጉን ገልጸዋል።

አገልግሎቱ ከመልካም አስተዳደርና ከሙስና ጋር ተያይዞ ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲነሳበት እንደነበር አስታውሰውም የጥቆማ አቀባበሉን በማዘመን ለቅሬታዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት ተጀምሯል ብለዋል።

ተቋሙ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ወስጥ ዘመናዊና የደንበኞችን ፍላጎት የሚያረካ እንዲሆን የጀመራቸውን ሥራዎች የበለጠ እንደሚያጠናክርም አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም