የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂክ እቅድ የሀገርን እድገትና ማንሰራራት እውን ለማድረግ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂክ እቅድ የሀገርን እድገትና ማንሰራራት እውን ለማድረግ ወሳኝ ነው
አሶሳ፤ ጥር 5/2018 (ኢዜአ)፦ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂክ እቅድ የሀገርን እድገትና ማንሰራራት እውን ለማድረግ ወሳኝ የልማት ዘርፍ መሆኑን የዘርፉ ምሁር ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ይፋ ሲያደርጉ በሰጡት ማብራሪያ ዲጂታል ኢትዮጵያ ፍትሐዊ እና አስተማማኝ እንዲሁም ትክክለኛ መረጃን ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የተገኘውን ስኬት በመሰነቅ በዘርፉ ልማት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችልና የሀገርን እድገትና ማንሰራራት የሚያረጋግጥ መሆኑ ይታመናል።
በመሆኑም ስትራቴጂክ እቅዱን ለማሳካት ከመንግሥት ጥረት ባለፈ የግሉ ዘርፍና አጠቃላይ የዜጎች የተቀናጀ ጥረትና ተሳትፎ ወሳኝ ይሆናል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት እና በኢንፎርሜሽን እና ኮሚዩኒኬሽን ኢንጂነሪግ ተባባሪ ፕሮፌሰር መልካሙ ደሬሳ (ዶ/ር)፤ ለዲጂታል ልማት መንግስት የሰጠው ትኩረት የዓለምን ነባራዊ እውነታ በተገነዘበ መልኩ መሆኑን ገልጸዋል።
የዲጂታል ቴክኖሎጂ ከዓለም ጋር ውድድር የሚገባበት በመሆኑ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ከመስራት ውጭ አማራጭ የሌለ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም መሰረት ያለፉት አምሰት ዓመታት ትግበራ እና ቀጣይ የተያዘው አቅጣጫ በብዙ መልኩ የኢትዮጵያን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ በዘርፉ ልማት ጥሩ መሰረት ያኖረ መሆኑን አንስተው የቀጣዩ ስትራቴጂክ እቅድ ደግሞ የላቀ ውጤት የሚመጣበት ስለመሆኑ አስረድተዋል።
በቀጣይ የአርቲፊል ኢንተለጀንስ እና ሌሎች ዘመን አመጣሽ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀምና በመወዳደር ለሀገር ልማትና እድገት መስራት ከሁላችንም ይጠበቃል ሲሉም አስገንዝበዋል።
የንግድ ስርዓቱን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ማድረግም አስፈላጊ መሆኑን አንስተው የመሶብ አንድ ማእከልን ማስፋት፣ ፋይዳን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ማድረግና የዲጅታል ግብይትን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስኬት የሚወሰነው በሁሉም ጥረትና ትብብር ሲሆን በተለይም የኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢንተርኔት አገልግሎትን ማስፋት ወሳኝ ይሆናል።