ቀጥታ፡

ከማላጋ እስከ አፍሪካ ዋንጫ፤ የሞሮኮው አዲስ እንቁ ብራሂም ዲያዝ

 

የግል ክህሎት፣ ፈጣን አስተሳሰቡ እና በጠባብ ክፍተቶች ውስጥ ሰብሮ የመግባት አቅሙ ሙገሳ እንዲጎርፍለት አድርጓል።

አንድ ለአንድ ሲገናኝ ተከላካዮችን በፈጣን አካላዊ ቅልጥፍና እና በድንገት አቅጣጫ በመቀየር የሚያልፍበት መንገድ እንዲሁም የመፍጠር አቅሙ የተመልካቾችን ቀልብ የሚይዝ ነው።

የአማካይ እና የአጥቂ መስመርን በማገናኘት እና በአስገራሚ ሁኔታ አጭር ኳሶችን በማቀበልም የተዋጣለት ተጫዋች ነው ማለት ይቻላል።

በቦታ አያያዙ የእግር ኳስ ልኅቀቱ ከፍተኛ ነው የሚል አድናቆት ከእግር ኳስ ባለሙያዎች አግኝቷል። ኳስን ሲያንከባልልም ለዐይን ይስባል።

ከክህሎቱ እና ከማራኪ እንቅስቃሴው ባለፈ ወደ ኋላ እየመለሰ ተከላካዮችን ያግዛል፣ ኳስ ይነጥቃል።

ይህ ተጫዋች የ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ክስተት የሆነው የሞሮኮው ብራሂም ዲያዝ ነው።

የ26 ዓመቱ የሪያል ማድሪድ የክንፍ መስመር ተጫዋች ዲያዝ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ አምስት ጨዋታዎችን አድርጎ አምስት ግቦችን በማስቆጠር የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ነው።

አዘጋጇ ሞሮኮ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ መክፈቻ ኮሞሮስን 2 ለ 0 ስታሸንፍ የውድድሩን የመጀመሪያ ግብ አስቆጥሯል።


 

ብራሂም አብዱልቃድር ዲያዝ የተወለደው እ.አ.አ ኦገስት 3 ቀን 1999 በስፔን ማላጋ ግዛት ነው። እናቱ ስፔናዊ አባቱ ሞሮኳዊ ናቸው።

ዲያዝ ያደገው በማላጋ ነው። እግር ኳስንም በአንዳሉሺያዊቷ ከተማ ሲጫወት ቆይቷል።

በ16 ዓመቱ ካደገበት ማላጋ በመውጣት እ.አ.አ በ2015 ወደ ማንችስተር ሲቲ ወጣት አካዳሚ በ200 ሺህ ፓውንድ ወጪ ተዘዋወረ።

ዲያዝ እ.አ.አ ሴፕቴምበር 21 ቀን 2016 በካራባኦ ካፕ (በቀድሞ አጠራሩ ሊግ ካፕ) ማንችስተር ሲቲ ከስዋንሲ ሲቲ ባደረገው ጨዋታ በ80ኛው ደቂቃ በኬሌቺ ኢናቺዩ ተቀይሮ በመግባት ለውኃ ሰማያዊዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጓል።

የመጀመሪያውን ጨዋታ ካደረገ ከሶስት ቀናት በኋላ ከማንችስተር ሲቲ ጋር ለሶስት ዓመታት የሚያቆየውን ፕሮፌሽናል ኮንትራት ተፈራርሟል።

እ.አ.አ ኖቬምበር 21 ቀን 2017 ማንችስተር ሲቲ ከፌይኖርድ ሮተርዳም ጋር ባደረገው የሻምፒዮናስ ሊግ ጨዋታ ላይ የመጀመሪያ የአውሮፓ መድረክ ጨዋታውን ማድረግ ችሏል።

በወቅቱ ብራሂም ስተርሊን መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪ ሰዓት ላይ ነበር ተቀይሮ የገባው።

ዲያዝ በውኃ ሰማያዊዎቹ ማልያ ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ገብቶ የተጫወተው እ.አ.አ ዲሴምበር 19 ቀን 2017 ነው። ማንችስተር ሲቲ ከሌስተር ሲቲ በካራባኦ ካፕ ጨዋታ ላይ ለ88 ደቂቃዎች ተሰልፎ ተጫውቷል።


 

እ.አ.አ ጃንዋሪ 20 ቀን 2018 ማንችስተር ሲቲ ኒውካስትል ዩናይትድን 3 ለ 1 ባሸነፈበት ጨዋታ በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጓል።

በወቅቱ ማንችስተር ሲቲ የሊጉን ዋንጫ ያነሳ ሲሆን፤ በውድድር ዓመቱ አራት ጨዋታዎች ላይ ብቻ ተሳትፎ ያደረገው ብራሂም ዲይዝ የሜዳሊያ ሽልማት አግኝቷል።

እ.አ.አ ኦገስት 5 ቀን 2018 ማንችስተር ሲቲ ቼልሲን 2 ለ 0 ባሸነፈበት የኮሙዩኒቲ ሺልድ ጨዋታ ላይ በፊል ፎደን ተቀይሮ በመግባት ለ15 ደቂቃዎች ተጫውቷል።

ዲያዝ እ.አ.አ 2018/19 ማብቂያ ላይ ማንችስተር ሲቲ ፉልሃምን 2 ለ 0 ባሸነፈበት ጨዋታ ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ የመጀመሪያ ግቦቹን ለሲቲ አስቆጥሯል።

በማንችስተር ሲቲ ያለው ውል እ.አ.አ 2019 ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ወቅት ስሙ ከዝውውር ጋር በስፋት ይነሳ ነበር።

ዲያዝ እ.አ.አ ጥር 2019 በ17 ሚሊዮን ዩሮ ከማንችስተር ሲቲ ወደ ሪያል ማድሪድ ተዘዋወረ። ለስድስት ዓመታት የሚያቆየውን ውልም ፈርሟል።

የክንፍ ተጫዋቹ የመጀመሪያ ጨዋታውን በነጮቹ ማልያ ያደረገው እ.አ.አ ጥር 9 ቀን 2019 ሪያል ማድሪድ ሌጋኔን በስፔን ጥሎ ማለፍ ዋንጫ 3 ለ 0 ባሸነፈበት ወቅት ነው።

ከአራት ቀናት በኋላ በስፔን ላሊጋ ሪያል ማድሪድ ሪያል ቤቲስን 2 ለ 1 ባሸነፈበት ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጓል።

የመጀመሪያ ግቡን ለማስቆጠር ሶስት ወራትን ጠብቋል። እ.አ.አ ግንቦት 12 ቀን 2019 ሪያል ማድሪድ በላሊጋው በሪያል ሶሲዬዳድ 3 ለ 1 ሲሸነፍ ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል።

በወቅቱ ዲያዝ ስድስት ጨዋታዎች ላይ በላሊጋው የተጫወተ ሲሆን፤ በመጀመሪያ ዓመቱ የሊጉን ዋንጫ አንስቷል።

ሪያል ማድሪድ እ.አ.አ በ2021/21 የውድድር ዓመት ብራሂም ዲያዝ ወደ ኤሲ ሚላን በውሰት ማምራቱን ይፋ አደረገ።

ዲያዝ ሚላን እ.አ.አ መስከረም 27 ቀን 2020 ክሮቶኔን 2 ለ 0 ባሸነፈበት ጨዋታ የመጀመሪያ ግቡን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

እ.አ.አ ግንቦት 2021 ኤሲ ሚላን ጁቬንቱስን 3 ለ 0 ሲያሸንፍ ያስቆጠረው ግብም ተጠቃሽ ነው።

ዲያዝ በኤሲ ሚላን የውሰት ውሉ ሲያበቃ በድጋሚ ለሁለት ዓመታት በውሰት የሚቆይበት ስምምነት ሪያል ማድሪድ ከጣልያኑ ክለብ ጋር የተፈራረመ ሲሆን፤ ውሉ ሚላን ተጫዋቹን የማቆየት መብት ሰጥቶታል።

እ.አ.አ መስከረም 15 ቀን 2021 ኤሲ ሚላን በሻምፒዮንስ ሊጉ የ3 ለ 2 ሽንፈት ሲያስተናግድ የመጀመሪያ የአውሮፓ መድረክ ግቡን አስቆጥሯል።

በ2023 ኤሲ ሚላን ቶተንሃም ሆትስፐርስን በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ 1 ለ 0 ሲያሽንፍ ብቸኛውን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።

እ.አ.አ በ2023 ሰኔ ወር ላይ ሪያል ማድሪድ ዲያዝ ከኤሲ ሚላን የሶስት ዓመታት የውሰት ቆይታ በኋላ ወደ ክለቡ መመለሱን አሳውቋል። 

ተጫዋቹ በኤሲ ሚላን ቆይታው 91 ጨዋታዎችን አድርጎ 13 ግቦችን ከመረብ ጋር አገናኝቷል።

ዲያዝ ወደ ሪያል ማድሪድ ከተመለሰ በኋላ ኮንትራቱን እስከ 2027 አራዝሟል።

እ.አ.አ መስከረም 27 ቀን 2023 ወደ ክለቡ ከተመለሰ በኋላ ሪያል ማድሪድ ላስ ፓልማስን 2 ለ 0 ባሸነፈበት ጨዋታ ግብ አስቆጥሯል።


 

የክንፍ መስመር ተጫዋቹ ሪያል ማድሪድ በሀገር ውስጥ እና በአውሮፓ መድረክ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ግብ በማስቆጠር እና ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።

ዲያዝ እስከ አሁን ለሪያል ማድሪድ ባደረጋቸው 129 ጨዋታዎች 20 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል። ከነዚህም ውስጥ 13ቱ በላሊጋው ያስቆጠራቸው ናቸው።

ከክለብ ወጣ ስንል የተጫዋቹን የብሔራዊ ቡድን ቆይታ እናገኛለን። ዲያዝ በታዳጊነቱ በተለያዩ የእድሜ እርከኖች ለስፔን ወጣት ቡድኖች ተጫውቷል።

እ.አ.አ በ2016/17 የውድድር ዘመን ለስፔን ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በ16 ዓመቱ ተሰልፎ መጫወት ችሏል።

በተለይም አዘርባጃን እ.አ.አ በ2017 ባዘጋጀችው 15ኛው የአውሮፓ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ ያሳየው ድንቅ ብቃት አድናቆት አስችሮታል።

በዚያ ቀጥለው በነበሩ ዓመታትም ለስፔን ከ19 እና ከ21 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች ተጫውቷል።

ብራሂም ዲያዝ በስፔን ታዳጊና ወጣት ቡድኖች ላይ በአጠቃላይ 28 ጨዋታዎችን አድርጎ ስድስት ግቦችን አስቆጥሯል።

የስፔን ታዋቂ የስፖርት ጋዜጣ ማርካ እ.አ.አ ጥር 23 ቀን 2023 ለሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን መጫወት ማቀዱን የሚመለከት ዘገባ ይዞ ወጥቷል። ከዜግነቱ ጋር በተያያዘ ያሉ አንዳንድ የአስተደዳር ጉዳዮች በወቅቱ መፍትሄ አግኝተዋል።

ይሁንና ኮትዲቯር እ.አ.አ በ2023 ባዘጋጀችው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሞሮኮው አሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉዊ ከተጫዋቹ ጋር በተደረገ የቅድሚያ ስምምነት ለተጫዋቹ ጥሪ አልተደረገለትም።

ዲያዝ እ.አ.አ መጋቢት 10 ቀን 2024 ለሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሀገሪቷ ብሔራዊ መጫወት እንደሚፈልግ በይፋ ማሳወቁን ማርካ በወቅቱ ዘግቧል። ጥያቄውም ተቀባይነት አገኘ።

በወቅቱ የሞሮኮ አሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉዊ ብሔራዊ ቡድኑ ከአንጎላ እና ሞሪታኒያ ጋር ለነበረበት የወዳጅነት ጨዋታ ለዲያዝ ጥሪ አድርገውለታል።

እ.አ.አ መጋቢት 22 ቀን 2024 ሞሮኮ አንጎላን 1 ለ 0 ባሸነፈችበት ጨዋታ ለብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጓል።

እ.አ.አ ጥቅምት 6 ቀን 2024 ሞሮኮ ለ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከጋቦን ጋር ባደረገችው ጨዋታ 4 ለ 1 ስታሸንፍ የመጀመሪያ ግቡን ለሞሮኮ ማስቆጠር ቻለ።

እ.አ.አ ሕዳር 15 ቀን 2024 ሞሮኮ በማጣሪያው ጋቦንን 5 ለ 1 ስትረታ ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል።

ከሶስት ቀናት በኋላ ሞሮኮ ከሌሴቶ ጋር ባደረገችው የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታ 7 ለ 0 ስታሸንፍ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር በሀገሩ ማልያ የመጀመሪያ ሀትሪኩን ሰርቷል።

እ.አ.አ ጥቅምት 2025 ሞሮኮ ራባት ላይ ኮንጎ ሪፐብሊክን 1 ለ 0 በማሸነፍ በስፔን ከዚህ ቀደም በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ተይዞ የነበረውን 15 ተከታታይ ጨዋታዎችን የማሸነፍ ክብረ ወሰን በመስበር ወደ 16 ማድረስ ችላለች። በዚህ ታሪካዊ ጨዋታ ላይ ዲያዝ ተሰልፎ ተጫውቷል። የሞሮኮ ተከታታይ የማሸነፍ ጉዞ 19 ጨዋታዎች ደርሶ የነበረ ሲሆን በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከማሊ ጋር አንድ አቻ ስትለያይ አብቅቷል።


 

ሞሮኮ ለ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በማጣሪያ ብታልፍም አስቀድማ ውድድሩን እንድታዘጋጅ እድል አግኝታ የነበረው ጊኒ በዝግጅት ማነስ ምክንያት በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ከሁለት ዓመት በፊት አዘጋጅነቷ ተነጥቆ ለሞሮኮ ተሰጥቷል።

ሞሮኮ የዘንድሮውን ውድድር በደማቅ ሁኔታ እያካሄደች ትገኛለች። በውድድሩ ላይ ጎልተው ከታዩ ተጫዋቾች መካከል ብራሂም ዲያዝ ተጠቃሽ ነው።

በአፍሪካ ዋንጫው እስከ አሁን ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን አስቆጥሯል። በተሰለፈባቸው በእያንዳዱ ጨዋታዎች ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ለሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን በአምስት የአፍሪካ ዋንጫ ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ያስቆጠረ የመጀመሪያው ተጫዋች በመሆን አዲስ ታሪክ ጽፏል።

ሞሮኮ በሩብ ፍጻሜው ማሊን 2 ለ 0 ስታሸንፍ የመጀመሪያውን ጎል አስቆጥሯል። ሀገሩ ወደ ግማሽ ፍጻሜ እንድታልፍ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱንም እየመራ ይገኛል። ሞሮኮ በዚሁ ግስጋሴዋ ከቀጠለች ዲያዝ የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እና ኮከብ ተጫዋች የመሆን እድሉ ሰፊ ነው።

ሞሮኮ በግማሽ ፍጻሜው ከናይጄሪያ ጋር ረቡዕ ጥር 6 ቀን 2018 ዓ.ም በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ታደርጋለች። ዲያዝ በዚህ ጨዋታ ላይ ልዩነት ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።  

አንዳንድ የእግር ኳስ ተንታኞች ብራሂም ዲያዝ እ.አ.አ በ2026 ወጥነት ያለው ብቃት ማሳየት ከቻለ የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋችነት ሽልማቱን የሚወስድበት የለም እያሉ ይገኛሉ።

ሞሮኳውያን በተጫዋቹ ፍቅር ልባቸው ከንፏል። በየጨዋታው ዲያዝ ዲያዝ እያሉ ከፍተኛ ድጋፍ እና ሙገሳ እየሰጡት ይገኛሉ። እሱም በድንቅ ብቃቱ ምላሽ እየሰጣቸው ነው።

በተወለደበት ማላጋ ከተማ የጀመረው የእግር ኳስ ሕይወት በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የበለጠ አብቧል።

የሞሮኮው አዲሱ ኮከብ ብራሂም ዲያዝ ቀጣይ የእግር ኳስ ሕይወት በስኬት እና በድል የደመቀ እንደሚሆን ከአሁኑ ድንቅ ብቃቱ ተነስቶ መናገር ይቻላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም