ሰባተኛውን ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ማከናወን የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛውን ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ማከናወን የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦ ሰባተኛውን ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ማከናወን የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሀገር አቀፍ የሕግ አውጪዎች የጋራ ምክክር መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የጋራ የምክክር መድረኩ የመንግሥታት ግንኙነት ስርዓትን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1231/2013 መሰረት ይካሄዳል።
በፌዴራል መንግሥት ፖሊሲዎች ሕጎችና ስትራቴጂዎች ላይ ተቀራራቢ አፈፃፀም፣ የጋራ መግባባት፣ ማሕበራዊ ፍትህ፣ ዘላቂ ሰላምና መልካም አስተዳደር፣ ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት ጥበቃ እንዲሁም አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ያለመ ነው።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚህ ወቅት፣ ሀገር አቀፍ የሕግ አውጪዎች የጋራ ምክክር መድረክ ዘላቂ ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ የአንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በዘንድሮው የምክክር መድረክ ወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ተነስተው ከፌደራልና ከክልል ህግ አውጪዎች ጋር ውይይት ይደረግባቸዋል ብለዋል።
ሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ዝግጅትና የምክር ቤቶች ሚና፣ የፐብሊክ በጀትና የፋይናንስ ትንተና እና ጥናት ሰነድ እንዲሁም የሕግ ኦዲት ሰነድ ላይ ምክክር እንደሚደረግም ገልጸዋል።
መንግስት ሰባተኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የግብዓት አቅርቦትና ሚና በተመለከተ ምክክር ማድረጉን ተናግረዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የክልል ምክር ቤቶች የዘንድሮው ምርጫ ከስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በተሻለ እንዲፈጸም የማስተባበር ሚናችንን በብቃት መወጣት አለብንም ነው ያሉት።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በርካታ ሪፎርሞች ማድረጉን በማንሳት፤ የክትትልና ቁጥጥር፣ የህዝብ ውክልና ሥራ በብቃት መወጣት የሚያስችል ሥራ እያከናወነ መሆኑንም አክለዋል።
በዚህም ምክር ቤቱ የህግ ማዕከል በማቋቋም የሚወጡ ህጎች ከህገ መንግስቱ፣ ከዓለም አቀፍ ህጎች እና ቀድመው ከነበሩ ሀገራዊ ህጎች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውንና ተፈፃሚነታቸውን መከታተል የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል ብለዋል።
የሀገር አቀፍ የሕግ አውጪዎች የጋራ የምክክር መድረክ የጋራ ትርክትን መገንባትና ግልፅነትን መፍጠር የሚያስችል ምህዳር ማስፈን እንደሚያስችል ጨምረው ገልጸዋል።