በመዲናዋ እየተከናወነ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራ አካታች እና ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን የያዘ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ እየተከናወነ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራ አካታች እና ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን የያዘ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራ አካታች እና ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን የያዘ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
በአዲስ አበባ በሚገኙ ስምንት ወንዞች ላይ 47 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የወንዝ ዳርች ልማት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
ከንቲባዋ ይህን ያሉት በከተማዋ እየተገነቡ ከሚገኙ ስምንት የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች መካከል የቀበና እና የግንፍሌ ወንዞችን የሥራ ሂደት በገመገሙበት ወቅት ነው።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ወንዞች ለከተማ መቆርቆር፣ ለከተማ ውበት እና ለከተማ ልማት ዋና እና መሰረት ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።
ይሁንና በአዲስ አበባ ወንዞች የብክለት ችግር የሚፈጠርባቸው፣ የተለያዩ ወንጀለኞች የሚደበቁበት፣ የበሽታ መንስኤዎች በመሆን ብዙ ተጽእኖዎችና ችግሮች ሲያደርሱ መቆየታቸውን አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ ወንዞች ላይ በተደረገ ጥናት በመዲናዋ ብቻ 76 ወንዞች እንዳሉ ጠቁመው ወንዞቹ ከየመጸዳጃ ቤቱ ፍሳሽ የሚገባባቸው ሆነው መገኘታቸውን ነው የገለጹት።
በለውጡ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ወንዞቻችንን እናጽዳ ሸገርን እናስውብ በሚል አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበባ ከማድረግ ራዕይ ጋር በማስተሳሰር በ2012 ዓ.ም የወንዞች ዳርቻ ልማት መጀመሩን አስታውሰዋል።
ስራው አዲስ አበባ ውብ አበባ መሆን የምትችለው ወንዞች ከጸዱ እና ወደ ተፈጥሯዊ ማንነታቸው ከተመለሱ እና ከዳኑ ብቻ እንደሆነ በትልቅ መረዳት የተጀመረ እንደሆነም ነው ያስረዱት።
የወንዝ ዳርቻ ልማት በወቅቱ ለኢትዮጵያ አዲስ በመሆኑ የውጭ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ አስፈልጎ እንደነበር አመልክተዋል።
ፕሮጀክቱ በተጀመረ አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሁለት ኪሎ ሜትር የሚሆን ብቻ ልማት መከናወኑን ጠቅሰው በራሳችን ሀገር በቀል አቅም ለምን አንሰራም? በሚል የዛሬ ዓመት በአዲስ መልክ ስራው መጀመሩን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያውያን አቅም በስምንት ወንዞች ላይ የ47 ኪሎ ሜትር የውንዝ ዳርቻ ልማት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ከዚህ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ከእንጠጦ እስከ ፒኮክ ያለው መሆኑን ገልጸው የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እና መሰረተ ልማቶችን ሳይጨምር 21 ኪሎ ሜትር እንደሚረዝም ገልጸዋል።
ከእንጠጦ እስከ ፒኮክ ባለው የወንዝ ዳርቻ ውስጥ ሰባት ፓርኮች እንደሚገኙና ንግድን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን እንደሚሰጡም ተናግረዋል።
በአጠቃላይ የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራው አካታች እና ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን የያዘ መሆኑን አክለዋል።