በኢትዮጵያ የካንሰር ታማሚ ህፃናትን አክሞ የማዳን ምጣኔን ለማሻሻል በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የካንሰር ታማሚ ህፃናትን አክሞ የማዳን ምጣኔን ለማሻሻል በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የካንሰር ታማሚ ህፃናትን አክሞ የማዳን ምጣኔን ለማሻሻል በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ገለጹ።
የኢትዮጵያ የህፃናት ሄማቶሎጂና ኦንኮሎጂ ማህበር የምስረታ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ፤ የካንሰር ህክምናን ማስፋፋት የሚያስችል የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና ማዕከላትን የማስፋፋት፣ የካንሰር መከላከያ ክትባት ተደራሽነትን ማስፋት፣ የኬሞቴራፒ እና የጨረር ሕክምናዎችን የማስፋፋት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም የህፃናት የካንሰር ሕክምና አገልግሎትና ተደራሽነትን በማስፋት የኬሞቴራፒ፣ የጨረር ሕክምና እና የመድኃኒቶች ተደራሽነትን ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የህፃናት ሄማቶሎጂና ኦንኮሎጂ ማህበር መመስረቱ በኢትዮጵያ የህፃናት የካንሰር ህመምን የመከላከልና ሕክምናውን የማስፋፋት ስራዎች ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የህፃናት ሄማቶሎጂና ኦንኮሎጂ ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር አቤል ሀይሉ፤ የህፃናት የካንሰር ህክምና አገልግሎቶችን በማሻሻል የመዳን አቅም ለማጠናከር የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የዓለም አቀፍ የህፃናት ኦንኮሎጂ ሶሳይቲ ፕሬዝዳንት ጄኔፈር ጂል፤ የኢትዮጵያ ህፃናት የካንሰር ሕክምና ተደራሽነትን ለማስፋት በሚደረገው ጥረት አጋርነታቸውን እንደሚጠናክሩ ተናግረዋል።
በማህበሩ ምስረታ መርሃ ግብር ላይ በኢትዮጵያ በህጻናት የካንሰር ህክምና ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የህክምና ባለሙያዎች ዕውቅና ተሰጥቷል።
ዕውቅና ከተሰጣቸው መካከል በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ሺላ ዋይትዝማን፤ በኢትዮጵያ የህፃናት ካንሰር ሕክምና አገልግሎት ላይ ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በህፃናት የካንሰር ሕክምና ላይ የታየው ከፍተኛ መሻሻል አክሞ የማዳን ቁጥር እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህፃናት የደምና የካንሰር ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት ዶክተር ጋሻው አረጋ፤ የካንሰር ታማሚ ህፃናት በወቅቱ ከታከሙ ከፍተኛ የመዳን ዕድል አላቸው ብለዋል።