ቀጥታ፡

የውሃ ሃብት ሁሉንም የህይወት ዘርፍ የሚነካ ወሳኝ አህጉራዊ የህልውና ጉዳይ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2018(ኢዜአ)፦ የውሃ ሃብት ለአፍሪካውያን ሁሉንም የህይወት ዘርፍ የሚነካ ወሳኝ አህጉራዊ የህልውና ጉዳይ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።

39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤና 48ኛው የሥራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ከየካቲት 4 እስከ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ይካሄዳል።

የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤን አጀንዳ፣ የውሳኔ ሀሳብና ሪፖርት ለማዘጋጀት የሚደረገው 51ኛው የሕብረቱ አባል ሀገራት ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ ስብሰባ ዛሬ ተጀምሯል።


 

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ትኩረቱን በውሀ ላይ ያደረገ ነው።

የውሃ ሃብት ለአፍሪካውያን ሁሉንም የህይወት ዘርፍ የሚነካ ወሳኝ አህጉራዊ የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤና ኮፕ 30ን ለመከታተል ትክክለኛ ምርጫ ነው ብለዋል።

የኮፕ 32 በአፍሪካ ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ በመመረጧ ኩራት ይሰማናል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረትና የተባበሩት መንግሥታት ለጉባኤው ዝግጅት በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላምና ጸጥታ ዙሪያ ብዙም ለውጥ ባልታየበት ሁኔታ እንደሚካሄድ ገልጸው፤ በሱዳን፣ ሊቢያ፣ በሳህል ቀጣና እና በምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ያለው ችግር እስካሁን አልተፈታም ብለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን መፍትሔ እንዲያገኙ ለማስቻል በሰላምና ደህንነት የሪፎርም በጋራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ላይ የሚጣሉ የታሪፍ ገደቦች፣ የሚሰበሰበው ሀብት መቀነስና የጉዞ ክልከላዎች የዓለም ህግና ሥርዓቱን በመሸርሸር አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ መሆኑንም አንስተዋል።

በመሆኑም ይህንን ኢ-ፍትሐዊነት ለመከላከል በሕብረቱ አባል ሀገራት መካከል ትብብርና አንድነትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።


 

በአፍሪካ ሕብረት የአንጎላ ቋሚ ተወካይ እና 51ኛው የሕብረቱ አባል ሀገራት ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ ስብሰባ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሚጉኤል ቤምቤ በአፍሪካ ዘላቂ የውሃ ሀብት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ መሪ ሀሳብ ውኃን መሰረት ያደረገ መሆኑን በማንሳት፤ በአፍሪካ በውኃ ጉዳዮች ላይ የሚነሱ ግጭቶችን መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ይመክራል ብለዋል፡፡

የዚህን መሪ ሀሳብ አመንጪ ኢትዮጵያ መሆኗን ያስታወሱት ፕሮፌሰር ሚጉኤል፤ ለአፍሪካውያን የቀረበ ሀሳብ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ ቀጣናዊ ትብብርና ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለመፍጠር የኢንዱስትሪ አብዮት ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና በሁሉም አባል ሀገራት ገቢራዊ መደረግ አለበት ነው ያሉት፡፡

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 አካል ነው ያሉት ፕሮፌሰር ሚጉኤል፤ አህጉራዊ ግቦችን ለማሳካት ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም