ቀጥታ፡

በክልሉ የተሻሻለው የገጠር መሬት አዋጅ ዘመናዊ አሰራርን ለመከተልና የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፋይዳው የላቀ ነው

ባህርዳር፤ ጥር 4/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የተሻሻለው የገጠር መሬት አስተዳደር አዋጅ ዘመናዊ አሰራርን ለመከተልና የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፋይዳው የላቀ መሆኑን የክልሉ መሬት ቢሮ ገለጸ።

‎የቢሮ ኃላፊው ሲሳይ ዳምጤ፤ የተሻሻለውን የገጠር መሬት አስተዳደር አስፈላጊነትና ጠቀሜታ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የተሻሻለው አዋጅ የገጠር መሬት ምዝገባ መረጃ ጥራቱን በጠበቀ አግባብ እንዲደራጅ ለማድረግና ለተጠቃሚ አርሶ አደሮች በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም ዘመናዊ የመሬት አያያዝ ስርዓትን ለመዘርጋት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

አዋጁ አርሶ አደሩ የእርሻ መሬቱን ለልጆቹና ለስጋ ዘመዶቹ በውርስና በስጦታ እንዲያስተላልፍ መብት የሰጠ መሆኑን አንስተው በጋራ የመንገድ፣ የመብራት፣ የቴሌኮምና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።

አርሶ አደሩ ከአበዳሪ ተቋማት ብድር መውሰድ የሚያስችል እንዲሁም ዘመናዊ አሰራርን ተግባራዊ ለማድረግና የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፋይዳው የላቀ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአዋጁ መሰረት አርሶ አደሩ መሬትን የመጠቀም መብት እንዳለው ሁሉ በአግባቡ ጠብቆና ተንከባክቦ ካልያዘ ደግሞ ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ መሬቱን እስከመንጠቅ የሚደርስ እርምጃ እንዲወሰድ የሚያደርግ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

የግል፣ የመንግስትና የወል መሬትን ወሮ የተገኘ ከ30ሺህ ብር እስከ 100ሺህ ብር ወይም ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት እስራት እንደሚቀጣ የሚደነግግ ሲሆን ሀሰተኛ የመሬት ማስረጃ ያቀረበም ከአንድ አመት እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ እስራት የሚቀጣ ይሆናል።

የተሻሻለው የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ባለፈው ወር አጋማሽ በተካሄደው የክልሉ ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ጉባኤ ፀድቆ ስራ ላይ መዋሉ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም