የጋራ ትርክት መገንባት ለነገው ትውልድ የምትመች ሀገር መፍጠር ማለት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጋራ ትርክት መገንባት ለነገው ትውልድ የምትመች ሀገር መፍጠር ማለት ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2018(ኢዜአ)፦ የጋራ ትርክት መገንባት ለነገው ትውልድ የምትመች ሀገር መፍጠር ማለት መሆኑን አምባሳደር ሌንጮ ባቲ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የጋራ ሀገራዊ ትርክቶችን ለመቅረጽ ያለመ ኮንፍረንስ በጅማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
አምባሳደር ሌንጮ ባቲ በኮንፍረንሱ ባቀረቡት የመወያያ ጽሑፍ የጋራ ትርክት መገንባት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በማምጣት መወያየትና መነጋገር እንደሚገባ ጠቁመው፤ ምክክር ማድረግ ሁነኛ አማራጭ ነው ብለዋል።
አንድነትን፣ አብሮነትንና እኩልነትን የሚያጎላ ትርክት መቅረጽ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሚያስተሳስሩ እና ዘመን ተሻጋሪ አብሮነቶችና ትስስሮችን ማጉላት የሚያስችል ትርክትን መገንባት እንደሚገባም ገልጸዋል።
የጋራ ትርክት መገንባት ለነገው ትውልድ የምትመችና የበለጸገች ኢትዮጵያን መፍጠር መሆኑንም አንስተዋል።
"ሀገራዊ ማንነት፣ የጋራ ትውስታዎችና የሀገረ መንግሥት ቅቡልነት፤ የኢትዮጵያ ተሞክሮ እና የመገናኛ ብዙኃን ሚና" በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረበችው ሙኒራ አብዱልመናን መገናኛ ብዙኃን የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደትን በማሳለጥና የዜጎችን የጋራ ማንነት በመቅረጽ ረገድ የጀርባ አጥንት መሆናቸውን ተናግራለች።
መገናኛ ብዙሃን ከአግላይና ነጣጣይ ትርክቶች ይልቅ የወል ትርክቶችን እና እሴቶችን ማጉላት እና ማስተጋባት እንደሚገባቸው ገልጻለች።
መገናኛ ብዙኃን ለብሔራዊ መግባባት ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባም ጨምራ ተናግራለች።
የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችም ስለ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸው ግንዛቤ ሊያድግ እንደሚገባ በመግለጽ፤ ለትውልድ የሚሻገር አስተሳሳሪ ትርክት ለመገንባት መትጋት እንደሚገባቸውም አንስታለች።
በመድረኩ በኢትዮጵያ የጋራ ትርክትን ተቋማዊ ለማድረግ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ሰፊ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።