ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ የሚያጸኑ አስደማሚ የልማት ስኬቶች እየተመዘገቡ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2018(ኢዜአ)፦ በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ የሚያጸኑ አስደማሚ የልማት ስኬቶች መመዝገባቸውን የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የበጀት ዓመቱን ያለፉት ስድስት ወራት የልማት አፈፃጸም አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ፥ 2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዓመት ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራትም የኢትዮጵያን ማንሰራራት የሚያጸኑ አስደማሚ የልማት ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በብዝኅ የኢኮኖሚ ዘርፍ በ2030 ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት የሚያደርጉ የልማት ስኬቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የመደመር መንግሥት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያም በሁሉም መስኮች ችግሮችን በማረም የኢትዮጵያን ዕድገት የሚያሳልጥ ውጤት መመዝገቡን አብራርተዋል።

በዚህም በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ዲጂታል ብዝኅ የኢኮኖሚ መስኮች እመርታዊ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የመደመር መንግሥት እሳቤ በግብርና መስክ በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በኩታ ገጠምና በሌማት ትሩፋት የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ተመጽዋችነትን የሚገታ የምርት ውጤት እየተገኘ መሆኑን አንስተዋል።

የጉባ ብስራት ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።

ከተሞችን የብልጽግና ማዕከል ለማድረግ በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደርና የወንዝ ዳር ልማትም በበርካታ ከተሞች በስፋት እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት የጉባ ብስራት ፕሮጀክቶች ጅማሮም ኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ጀምራ ማጠናቀቅ እንደምትችል የሚያሳዩ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ስኬትና የጉባ ብስራቶች ጅማሮ የመደመር መንግስት አካታችነትንና የኢትዮጵያን ዕድገት መሻት ለዓለም መድረክ የሚያረጋግጡ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ግንባታው በይፋ የተጀመረው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያም የኢትዮጵያን ርዕይ የገለጠ የማንሰራራት ተምሳሌት ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያና አፍሪካውያንን የአይችሉም ስብራት የደፈቀ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ ፕሮጀክቱም ኢትዮጵያን የወደፊቷ የአፍሪካና የዓለም ዋነኛ የአየር ትራንስፖርት በር ያደርጋታል ብለዋል።

የዓለም አቀፍ አየር ማረፊው የአፍሪካውያንን ሁለንተናዊ ትስስር በማጠናከር አዳዲስ የኢኮኖሚ ዕድሎችን የሚያሰፋ ዘመናዊ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሥርዓት የሚፈጥር መሆኑንም አስረድተዋል።

በዲፕሎማሲ መስክም በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች የኢትዮጵያ ተሳትፎም ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ የአፍሪካ ድምጽ መሆን ያስቻለ ስኬት መመዝገቡን ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የአፍሪካ ትርክትና ዕይታን የሚያንጸባርቅ አህጉራዊ ሚዲያ አስፈላጊነት በመገንዘብ ፐልስ ኦፍ አፍሪካ(POA) የተሰኘ ሚዲያ ማስጀመራቸውን አስታውሰዋል።

ሚዲያው የአፍሪካን ድምፅና መሻት በማጉላት የአፍሪካውያንን ትስስርና አህጉራዊ ስኬቶች፣ ተግዳሮቶችንና ሕልሞችን በአፍሪካዊ ዕይታ ወደ መግለጥ መሸጋገሩን አብራርተዋል።

በመንግስትና ሕዝብ መካከል የተደረጉ መድረኮችም ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው የልማት ስኬት ዕውቅና የተሰጠበትና የህዝብና መንግስት መተማመን የተፈጠረበት መሆኑንም አብራርተዋል።

በዚህ ዓመት የሚካሄዱት የሀገራዊ ምክክርና ሀገራዊ ምርጫ ዐበይትና ወሳኝ ሁነቶችን በአሳታፊነት፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ በስኬት ለማስኬድም መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም