ከክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት 33ሺህ 700 ቶን የቡና፣ ሻይ እና ቅመማቅመም ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል - ኢዜአ አማርኛ
ከክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት 33ሺህ 700 ቶን የቡና፣ ሻይ እና ቅመማቅመም ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል
ቦንጋ፤ ጥር 4/2018(ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 33ሺህ 700 ቶን የቡና፣ ሻይ እና ቅመማቅመም ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡ ተመለከተ።
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ የሺዋስ ዓለሙ፤ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትንና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
በተለይም በግብርናው ዘርፍ በዋና ዋና ሰብሎች እንዲሁም በቡና፣ ሻይ እና ቅመማቅመም ምርቶች ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
በዚህም መሰረት በክልሉ በዋና ዋና ሰብሎች 384 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት ከ20 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት 33 ሺህ 700 ቶን የቡና፣ ሻይ እና ቅመማቅመም ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ጠቁመው ከቀረበው ውስጥ 13ሺህ ቶኑ ቡና፣ 2ሺህ 700 ቶኑ ሻይ እና 18 ሺህ ቶኑ ቅመማቅመም መሆኑን አመልክተዋል።
በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከ255 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መቅረቡንም ጠቁመዋል።
በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ አገልግሎትና ሌሎች ዘርፎች ለተሰማሩ 52 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል።
በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርም በርካቶች ተሰማርተው ስኬታማ መሆናቸውንና ለሌሎችም ጭምር የስራ ዕድል መፍጠራቸውን አንስተዋል።
የውሃ፣ የመስኖ፣ የመንገድና ድልድዮችን፣ እንዲሁም የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎች ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ መሰረተ ልማቶች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም በከተሞች ፈጣንና ቀልጣፋ የዲጂታል አገልግሎት በመስጠት በኩል መልካም ጅምሮች መኖራቸውን አንስተው በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።