ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የህግ የበላይነትን በማስከበር የልማት ስራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ

ጋምቤላ፤ ጥር 4/2018(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል የህግ የበላይነትን በማስከበር የልማት ስራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።

የጋምቤላ ክልል የመንግስት ሰራተኞች በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ የውይይት መድረክ አካሂደዋል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ፤ በክልሉ የህግ የበላይነትን በማስከበር የልማት ስራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት የመንግስት ሰራተኞች ተሳትፎ እና ትብብር ወሳኝ መሆኑን አንስተው በሁሉም ረገድ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠልና የአገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

የሚነጣጥሉ እሳቤዎችን በመተው አሰባሳቢና የወል ትርክቶችን በመገንባት ረገድም የመንግስት ሰራተኞች የላቀ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የሚጥሩ አካላትን በመከታተል በህግ ተጠያቂ የማድረግ፣ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥና የልማት ስራዎችን ለስኬት የማብቃት ጉዳይ በቀጣይ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን(ዶ/ር) የክልሉ መንግስት የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ የልማት ስራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የሁሉም ድጋፍና ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አንስተው በተለይም የመንግስት ሰራተኞች የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አሽኔ አስቲን፤ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነትን በማጠናከር ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ የመንግስት ሰራተኞችም ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና የልማት ስራዎች መሳካት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በጋምቤላ ክልል ለልማት የሚውል እምቅ የተፈጥሮ ሀብት መኖሩን አንስተው በጋራ በመስራትና በማልማት ጥቅም ላይ የማዋል ስራ እንዲሳካ እንሰራለን ብለዋል።

#Ethiopian_News_Agency

#ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም