የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለልማት ሥራዎች ስኬታማነት የሚያበረክቱትን አስተዋጾ ማጠናከር አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለልማት ሥራዎች ስኬታማነት የሚያበረክቱትን አስተዋጾ ማጠናከር አለባቸው
ወላይታ ሶዶ፤ ጥር 4/2018(ኢዜአ)፡-የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሀገራዊ የልማት ሥራዎች ስኬታማነት በቅንጅት የሚያበረክቱትን አስተዋጾ ማጠናከር እንዳለባቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አስታወቀ።
14ኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና የፌደራልና የክልል ባለድርሻ አካላት የጋራ ጉባኤ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።
"የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ትብብርና ቅንጅት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው መድረክ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደገለጹት፣ ድርጅቶቹ ለሀገራዊ ልማትና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያላቸው የላቀ ሚና ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
በተለይ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎች ስኬታማነት እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው ማስቀጠል አንዳለባቸው ጠቅሰው፣ ለዚህም ከመንግስት ጋር ይበልጥ ተቀራርበው እንዲሰሩ ከማድረግ ባለፈ አሰራሮችን የማዘመን ሥራ ይሰራል ብለዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት ጠንካራ ስርአት ለመዘርጋት ሲሰራ መቆየቱንና በዚህም ውጤት መመዝገቡን አመልክተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በክልሉ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት ሥራዎችና እድገት ስኬታማነት የሚያደርጉት አስተዋጾ የላቀ መሆኑን አንስተዋል።
ድርጅቶቹ በክልሉ ሚናቸውን በተቀናጀ መንገድ እንዲወጡም የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀትና ምክር ቤት በማቋቋም በተቀናጀ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በክልሉ የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎቶች በማገዝ ረገድ እያበረከቱት ያለው አስተዋጾ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ያሉት አቶ ገብረመስቀል ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠልም ይሰራል ብለዋል።
ድርጅቶቹ በክልሉ የበጎ ፍቃደኝነት እና የበጎ አድራጊነት ባህልን በማጎልበትና በማስረጽ በልማትና በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በክልሉ ከ15 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ 132 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዳሉ ያነሱት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ ናቸው።
ድርጅቶቹ ከ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን በተለያዩ የልማት ሥራዎች ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
ይህን አበርክቶ ለማጠናከር የትብብርና የክትትል ስራው ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸው፣ የድርጅቶቹ የአጋርነት ሚና እያደገ መምጣቱንም አስታውቀዋል።
በመድረኩ ከፌደራልና ከክልሎች የመጡ ባለድርሻ አካላት፣ የፍትህና የፋይናንስ ቢሮዎች ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተሳትፈዋል።