ቀጥታ፡

በአዳማ ከተማ ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ ሆነዋል

አዳማ፤ ጥር4/2018 (ኢዜአ)፡- በአዳማ ከተማ ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደረገ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ተጠናከሮ መቀጠሉን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ደረጀ ተስፋዬ ለኢዜአ እንዳሉት በከተማ አስተዳደሩ በ116 ትምህርት ቤቶች የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው።

መርሃ ግብሩም በከተማ አስተዳደሩ ቡሳ ጎኖፋ፣ በህብረተሰቡ፣ በባለሀብቶች እና በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብሩ  ከ40 ሺህ በላይ የቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል።  

የትምህርት ቤት የምገባ መርሃ ግብሩ፣ የተማሪዎች  መጠነ ማቋረጥ መቀነስና የተማሪዎችን ውጤት ማሻሻል ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

ከዚህ አንጻር በከተማ አስተዳደሩ በ2017 የትምህርት ዘመን የ6ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች መካከል 93 በመቶ በላይ ወደ ቀጣዩ ክፍል ማለፋቸውን ተናግረዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ አቶ ዋዶ አብዱልከሪም በበኩላቸው ቡሳ ጎኖፋ  ለትምህርት ቤት ምገባ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ለተግባራዊነቱም ከህብረተሰቡና ከአጋር አካላት የምግብ እህልና ገንዘብ በማሰባሳብ መርሃ ግብሩን ማሳካት መቻሉን ጠቁመዋል።

በዚህም 42 ሺህ 456 ተማሪዎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው በቀጣይም ተግባሩን ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም