ቀጥታ፡

የጋራ ትርክት ለጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታና ለትውልድ ሽግግር ጉልህ ሚና አለው

አዲስ አበባ፤ጥር 4/2018 (ኢዜአ)፦የጋራ ትርክት ለጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታና ትውልድ ሽግግር ጉልህ ሚና እንዳለው የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ገለጹ።        

በኢትዮጵያ የጋራ ሀገራዊ ትርክቶችን ለመቅረጽ ያለመ ብሔራዊ ኮንፍረንስ በጅማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በኮንፍረንሱ ታዋቂው የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ "የጋራ የወል ትርክት ግንባታ እና ፈተናዎቹ" በሚል ርዕስ የመነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል።


 

በመነሻ ጽሑፋቸውም፤ ኢትዮጵያዊያን ከልዩነትና ነጣጣይ ትርክቶች ይልቅ በጋራ ትርክት ላይ በማተኮር ለጽኑ ሀገረ መንግሥት ግንባታ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

አግላይና ነጣጣይ ትርክት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ፈታኝ መሆናቸውን በመጥቀስ የዜጎችን አንድነትና አብሮነት የሚያጠናክር የወል ትርክት መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ የወል ትርክት ግንባታም በታሪክ ሂደት ውስጥ ያጋጠሙ ስብራቶችን በሚያርቅ አካሄድ አብሮነትን በሚያጸኑና ሁሉንም ወገኖች በሚያቅፉ የታሪክ እውነታዎች ላይ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

ምሁራን ታሪክን ለሀገረ መንግሥት ግንባታና ለሕዝቦች መቀራረብ እንዲውል የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።


 

የጋራ ትርክት ግንባታ ሂደቱንም በተሻለ የሃሳብ የበላይነት በመምራትም የተሻለችና አስተሳሳሪ ትርክት የነገሰባት ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የጋራ ትርክት ግንባታ ለጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታና ለተሻለ የትውልድ ሽግግር ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል።

በኮንፍረንሱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ  ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባኤ ሰዓዳ አብዱረህማን እና ሌሎች የፌዴራልና የክልል አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም