ቀጥታ፡

በክልሉ ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በመከላከል ገበያን የማረጋጋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

ሚዛን አማን፤ ጥር 4/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በመከላከል ገበያን ለማረጋጋት የተሰራው ሥራ ውጤታማ በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ታሪኩ አካሉ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሕገወጥ ንግድና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ የገበያ ዋጋን በማናር በዜጎችና በሀገር ላይ ጉዳት ያደርሳል።

ይህን ለማስቅረትም በክልሉ በህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ላይ የሚሳተፉ አካላትን ተከታትሎ እርምጃ በመውሰድ የመከላከል ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት በምርቶች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉና በሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይትና መሰል ተግባራት ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችን በመከታተል እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል። 

እንደኃላፊው ገለጻ፤ በገንዘብ ከተቀጡት ነጋዴዎች መካከል 1ሺህ 670 የሚሆኑት ለመንግስት ሠራተኞች የተደረገን የደመወዝ ማሻሻያን ተከትሎ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረጋቸው እርምጃ የተወሰደባቸው ናቸው።

በቀጣይም የተጋነነ የዋጋ ጭማሪና የምርት ስወራ እንዳይኖር በመከላከል ገበያን ለማረጋጋት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ገበያን ለማረጋጋት የተሰሩ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የገለጹት ሃላፊው፣ ህጋዊ የግብይት ስርዓቱን ለማጠናከርም ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። 


 

ከሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ወይንሸት ዘውዴ፤ መንግሥት በንግድ እንቅስቃሴው ላይ የሚፈጸሙ ህገወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ለሸማቹ መብት መከበር ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

አንዳንድ ነጋዴዎች በሕገ ወጥ መንገድ ለመክበር የሚያደርጉት ጥረት ሕዝብና ሀገር ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥር ገልጸው፣ በመንግስት ህገወጥነትን ለመከላከል ለሚሰሩ ሥራዎች በአቅማቸው ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም