ቀጥታ፡

በክልሉ የጤና አገልግሎትን በማዘመን የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ትኩረት ተሰጥቷል

ወራቤ ፤ ጥር 4/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጤና አገልግሎትን ዲጂታላይዝ በማድረግ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጎልበት ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ በጤናው ስርዓት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ያለመና ለዘርፉ ከፍተኛ አመራሮች የተዘጋጀ ስልጠና ዛሬ በወራቤ ከተማ መሰጠት ተጀምሯል።  

"ጠንካራ የአመራር ስርዓት ግንባታ ለውጤታማ የጤና ስርዓት" በሚል መሪ ሀሳብ እየተሰጠ ያለው ስልጠና ከዛሬ ጀምሮ ለስምንት ቀናት እንደሚቆይ ታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ በጤናው ዘርፍ ጠንካራ የአመራር ስርዓት በመፍጠር የላቀ እመርታ ለማስመዝገብ እንዲቻል ታስቦ ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በክልሉ በጤናው ሥርዓት ላይ የተስተዋሉና በጥናት የተለዩ ችግሮችን በማረም ቀልጣፋና ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።


 

የጤና አገልግሎት ስርዓቱን በቴክኖሎጂ በማገዝ አገልግሎቱን ከማዘመን ባለፈ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጎልበት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ወቅቱ የደረሰበትን ደረጃ የሚመጥን የጤና  አገልግሎት ለማህበረሰቡ በፍትሀዊነት ተደራሽ ለማድረግ ባለፉት ስድስት ወራት  ሁለት አጠቃላይ ሆስፒታሎችን ጨምሮ በአምስት የጤና ተቋማት ከወረቀት ነፃ የሆነ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ መደረጉንም ነው የገለጹት። 

ዛሬ የተጀመረው ስልጠናም የጤና አገልግሎት ስርዓቱን በዲጂታላይዝ በማገዝ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ  የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።

ከክልሉ መንግስትና ከጤና ሚኒስቴር ድጋፍ በተጨማሪ ማህበረሰቡን በማስተባበር በጤና ተቋማት ግንባታ፣ በመድኃኒት አቅርቦትና በህክምና ግብዓቶችን ማሟላት ላይ የተሰራው ስራ  ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑንም አቶ ሳሙኤል አክለዋል፡፡

ለዚህም በ71 ጤና ተቋማት የአልትራሳውንድ ሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉንና በክልሉ የኮምፕሬሄንሲቭ ጤና ኬላዎችን ተደራሽነት ለማስፋት እየተሰራ ያለውን ስራ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በክልሉ ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብን ለመፍጠር የተጀመረውን ሥራ ለማጠናከር አመራሩ ማህበረሰቡን በማስተባበርና በአካባቢው የሚገኝን ሀብት በመጠቀም በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት እንዲያስመዘግብ ስልጠናው አጋዥ መሆኑም አመልክተዋል

ለተከታታይ 8 ቀናት በሚሰጠው ስልጠና ላይ ከተለያዩ የወረዳ መዋቅር የተውጣጡ ከ200 በላይ የጤና ዘርፍ አመራሮች  በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም