ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል በ32 ሺህ የችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች ችግኝ የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ ነው

አዳማ ፤ ጥር 4/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል በ32 ሺህ የችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች በክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር  የሚተከሉ ችግኞች  እየተዘጋጁ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የደን ልማትና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ከተማ አብዲሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርና የተፈጥሮ ልማትና ሀብት ስራ ለምርታማነት እንዲሁም ለአካባቢ ጥበቃ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።


 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተጎዱና የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ፣ የደረቁ ኃይቆች፣ ወንዞችና ጅረቶች እንዲመለሱ ማድረጉንም ገልጸዋል።

በተያዘው በጋ ወራትም በ32 ሺህ የችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች ለኢኮኖሚ፣ ለምግብነት ፣ለደን ሽፋንና ለውበት የሚውሉ ችግኞችን  የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ከችግኝ ማፊያ ጣቢያዎቹ ጎን ለጎን የክልሉ አርሶ አደሮችም በችግኝ ዝግጅቱ እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

በክልሉ ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር እየተዘጋጁ ካሉ ችግኞች ውስጥ ለፍራፍሬ፣ ለጥምር ደን አገልግሎት፣ ለአፈር ለምነትና ለውበት የሚውሉ 60 በመቶ ሲሸፍኑ ቀሪዎቹ  40 በመቶ  ለደን ሽፋን አገልግሎት እንደሚውሉ ገልጸዋል።

ባለፈው ክረምት ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ በመጀመሪያው ዙር ቆጠራ ከ90 በመቶ በላይ መጽደቁንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም