ቀጥታ፡

መንግስት ለባህል ጥበባትና ስፖርት ዘርፉ በሠጠው ልዩ ትኩረት ስኬታማ ስራዎችን መስራት ተችሏል- ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ

አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2018 (ኢዜአ)፦መንግስት ለባህል ጥበባትና ስፖርት ዘርፉ በሠጠው ልዩ ትኩረት ስኬታማ ስራዎችን መስራት ተችሏል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።

 የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር "የባህል፣ ጥበባትና ስፖርት ዕምርታ ለኢትዮጵያ ከፍታ!" በሚል መሪ ቃል የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሴክተር ጉባኤ እያካሄደ  ነው።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በጉባኤው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በባህል ጥበባትና ስፖርት ዘርፍ ባለፉት 6 ወራት የላቀ ስኬት መከናወኑን ገልፀዋል።


 

መንግስት ለስፖርት ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት ውድድሮችን በማስቀጠል፤ ነባሩን የስፖርት ፖሊሲ በማሻሻል ማፀደቅ እንዲሁም  በዓለምአቀፍ መድረክ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ አንስተዋል።

አጠቃላይ በሀገሪቱ ጥርጊያ ሜዳዎችን ጨምሮ 43 ሺህ 335 የይዞታ ማረጋገጫ ያላቸው ስፍራዎች ያሉ መሆኑን የገለጹ ሲሆን 15 ሺህ 796 ሜዳዎች ባለፉት 8 ዓመታት ብቻ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ያገኙ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።


 

ከጥበባት ዘርፍ አንፃር የኢትዮጵያን መልክ አጉልተው የሚያሳዩ የጥበብ ስራዎች የተሰሩበት፤ ታላላቅ ኮንፈረንሶችና መድረኮች የተካሄዱበት መሆኑም ተገልጿል።

የህዝብ እና የአደባባይ በዓላትን በመጠቀም የህዝብ ለህዝብ ትስስር የተፈጠረበት፤ የቋንቋና የበዓላት ፕሮፋይል የተሰነደበት፣ የጥናትና ምርምር ስራዎች ከባህልና ቋንቋ ዘርፍ አንፃር መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም