በአስተዳደሩ ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት የሚያሳልጥ የቴክኖሎጂ አሰራር አቅም ተገንብቷል - ኢዜአ አማርኛ
በአስተዳደሩ ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት የሚያሳልጥ የቴክኖሎጂ አሰራር አቅም ተገንብቷል
አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት የሚያሳልጥ የቴክኖሎጂ አሰራር አቅም መገንባቱን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ።
በአዲስ አበባ ከተማ 23 ወረዳዎች በኃይል መቆራረጥ የሚፈጠርን የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት ምላሽ የሚሰጥ የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
በዚሁ ጊዜ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤ የመዲናዋን ነዋሪዎች የተቋማት የአገልግሎት ፍላጎት እርካታ የሚያረጋግጥ ዘመናዊ አሰራር እየተዘረጋ ነው ብለዋል።
በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፈጠረው ዘመናዊ የቴክኖሎጂ የአሰራር ሥርዓት አቅም ለተገልጋዮች የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማሳለጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በወረዳዎች የተገነባው የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክትም በኃይል መቆራረጥ ምክንያት የሚፈጠርን የአገልግሎት ክፍተት ምላሽ በመስጠት የደንበኛ እርካታን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በተለይም በወሳኝ ኩነት ምዝገባ ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይል ሲቋረጥ ለሚፈጠሩ የአገልግሎት ክፍተቶች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚረዳ አስረድተዋል።
በቀጣይም የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች በአስተማማኝ የኃይል አቅርቦትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አሰራር የማስቀጠል ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ንጉሴ፤ የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቱ የወሳኝ ኩነት አገልግሎቶችን ለማሳለጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።
በቀጣይም አገልግሎት በሚበዛባቸው ወረዳዎች የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶችን በማስፋት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲያገኙ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ እሸቱ ለማ (ዶ/ር)፤ የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቱ በኃይል መቆራረጥ ምክንያት የሚፈጥርን የአገልግሎት ክፍተት አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንደሚረዳ ተናግረዋል።