በአፋር ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከ3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከ3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ
ሰመራ፤ ጥር 4/2018 (ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከ3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ አቶ አወል አብዱ፤ የበጀት ዓመቱን የስድስት ወራት የገቢ አሰበሰብ ሂደቱን አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
አቶ አወል በመግለጫቸው፤በበጀት ዓመቱ በስድስት ወራት ውስጥ 4 ቢሊዮን 78 ሚሊዮን 630 ሺህ ለመሰብሰብ ታቅዶ 3 ቢሊየን 998 ሚሊዮን 779 ሺህ ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
ገቢው የተሰበሰበው ቀጥታና ቀጥታ ካልሆኑ ታክሶችና ከሌሎች የገቢ አርዕስቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በግብር አሰባሰቡ የእቅዱን 98 በመቶ ማከናወን መቻሉን ገልፀው በቀጣይም የገቢ አሰባበሰብ ሂደቱን በማዘመን የክልሉን ልማት ለማሳካት ርብርብ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የገቢ አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫና የ50 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ሃላፊው አስረድተዋል።
በክልሉ ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብ የሚያስችል ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ በተሰሩ የንቅናቄና የግንዛቤ ማሳደግ ስራዎች ግብርን በጊዜ የመክፈል ሁኔታው እየተሻሻለ መምጣቱን ገልፀዋል።
በተለይም የግብር አሰባሰቡን ዲጂታላይዝ በማድረግ ግብር ከፋዩ በቀላሉ መስተናገድ እንዲችል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዘርፉ የተሻሉ አሰራሮችን በመዘርጋትና ህገ ወጥ ግለሰቦችን ወደ ህጋዊነት የማምጣት ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው፤ ወደ ትክክለኛው መንገድ መምጣት ባልቻሉት ላይ ደግሞ ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑንም አቶ አወል ገልጸዋል።