የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያዊያንን የሚያስተሳስር ገዥ ትርክት ለመገንባት በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያዊያንን የሚያስተሳስር ገዥ ትርክት ለመገንባት በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2018 (ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያዊያንን የሚያስተሳስር ገዥ ትርክት ለመገንባት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።
በኢትዮጵያ የጋራ ሀገራዊ ትርክቶችን ለመቅረጽ ያለመ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ በጅማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) "ሀገራዊ ማንነት፣ የጋራ ትውስታዎች እና የሀገረ መንግሥት ቅቡልነት፤ የኢትዮጵያ ተሞክሮና የተያዙ አሁናዊ አቅጣጫዎች" በሚል ርዕስ የመደመር መንግሥት ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የያዛቸውን ቁልፍ አቅጣጫዎች የሚያመላክት ጽሑፍ አቅርበዋል።
በመነሻ ጽሑፋቸውም፤ ኢትዮጵያ ጥንታዊት፣ የሥልጣኔ መገኛ፣ የዳበረ የሥነ-መንግሥት ልምምድ ያላት፣ የሊግ ኦፍ ኔሽን የመጀመሪያዋ አባልና የአፍሪካ ሕብረት መሥራች መሆኗን አስረድተዋል።
በ1888 ዓ.ም የዓድዋ ድልም የነፃነት ተምሳሌትነትን የተጎናጸፈች፣ በቋንቋ፣ በባህልና በማንነት ስብጥር የታደለች ብትሆንም የሀገረ መንግሥት ቅቡልነት ችግር ሌላኛው ፈታኝ ገጽታዋ ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያዊያን የጋራ ማንነትና ትውስታ በንግድ፣ በኃይማኖት፣ በፍልሰትና በተፈጥሮ አደጋዎች መስተጋብር መፈጠሩንም አብራርተዋል
የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ገና ያልተጠናቀቀ በመሆኑም የተረጋጋና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት መገንባት የሁሉንም ተሳትፎ እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።
ኋላቀር የፖለቲካ ባሕል፣ የተዛባ ትርክትና ጸጋዎችን በአግባቡ አለመጠቀም ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ቁልፍ ማነቆ ሆነው መቆየታቸውን አንስተዋል።
በዚህ መነሻነትም የመደመር መንግስት የኢትዮጵያን ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮች በዘላቂነት እልባት ለመስጠት በግልጽ አቅጣጫ በመተለም በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በዚህም ብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም፣ የብሔራዊነት ገዥ ትርክትና የሐሳብ ገበያ፣ የሃሳብ ፖለቲካና ኢትዮጵያ የመግባባት ዲሞክራሲ፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ አብራርተዋል።