በመጀመሪያው መንፈቀ-ዓመት 4 ነጥብ 854 ሺህ ቶን የሻይ ልማት ምርት ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በመጀመሪያው መንፈቀ-ዓመት 4 ነጥብ 854 ሺህ ቶን የሻይ ልማት ምርት ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፤ጥር 4/2018 (ኢዜአ)፡-በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ በባለሃብትና በአርሶ አደር ከለማው የሻይ ልማት 4 ነጥብ 854 ሺህ ቶን ምርት መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታውቋል።
በባለሃብትና በአርሶ አደር 6 ሺህ 396 ሔክታር በሻይ ልማት መሸፈኑን በባለሥልጣኑ የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ደፈረስ ለኢዜአ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ከለማው ውስጥ አሁን ላይ ምርት የሚሰጠው 4 ሺህ 936 ሔክታር መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ከዚህም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመቱ አጋማሽ 4 ነጥብ 854 ሺህ ቶን የሻይ ልማት ምርት መሰብሰቡን አረጋግጠዋል።
እስካሁን ባለው መረጃና ልየታ መሠረት በኢትዮጵያ ለሻይ ቅጠል ልማት ተስማሚና ምቹ የሆነ ከ6 ሚሊየን ሔክታር የሚልቅ መሬት መኖሩን አመላክተዋል።
ካለው የመልማት ዐቅም አንጻር እየለማ ያለው አነስተኛ መሆኑን አንስተው፤ በዘርፉ በቀጣይ የተሻለ ለመሥራት መንግሥት ትኩረት መስጠቱን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ የሻይ ቅጠል ወደ ተለያዩ ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቷን እንደምትደጉምም አንስተዋል።