የጋራ ትርክት ግንባታ የሕዝብን አብሮነት የሚያጠናክር የነገ ተስፋን የሚያንጽ ወሳኝ መሣሪያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጋራ ትርክት ግንባታ የሕዝብን አብሮነት የሚያጠናክር የነገ ተስፋን የሚያንጽ ወሳኝ መሣሪያ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2018 (ኢዜአ)፦ የጋራ ትርክት ግንባታ ስብራትን በመጠገን የሕዝብን አብሮነት የሚያጠናክር የነገ ተስፋን የሚያንጽ ወሳኝ መሣሪያ መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከፍያለው ተፈራ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የጋራ ሀገራዊ ትርክቶችን ለመቅረጽ ያለመ ሀገር አቀፍ ኮንፍረንስ በጅማ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የጋራ ትርክት ግንባታ የሕዝብን አብሮነትና አንድነት የሚያጠናክር የነገ ተስፋ መገንቢያ መሣሪያ ነው።
ነጣጣይ ትርክት ለሀገረ መንግስት ግንባታ እንቅፋት መሆኑን በመጠቆም፤ አሰባሳቢና የጋራ ትርክት ግንባታ ግን የሀገረ መንግስት ግንባታን በጽኑ መሰረት እንደሚያንጽ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ አሰባሳቢ ትርክት ግንባታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስብራቶችን በመጠገን ለዜጎች አብሮነትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ወሳኝ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በመደመር መንገድ በአሰባሳቢና የጋራ ትርክት ግንባታ በዜጎቿ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ስኬታማ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የኢትጵያዊያንን ሕብረ ብሔራዊ ትስስር የሚያሰናስሉ ዘላቂ የአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ ሥራዎችንም በስትራቴጂክ ፖሊስ ማስደገፍ ትኩረት የተሰጠው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የዜጎችን የወል ትርክት ግንባታ በጽኑ መሰረት ለማነጽ በሚደረገው ጥረትም ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ገንቢ ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አሰባሳቢና የወል ትርክት ግንባታ ለሀገረ መንግስት ግንባታ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያዊያንን የጋራና አሰባሳቢ ትርክት ግንባታ ላይ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በኮንፍረንሱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባኤ ሰዓዳ አብዱረህማን እና ሌሎች የፌዴራልና የክልል አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።