የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅና በመንከባከብ የለማች ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅና በመንከባከብ የለማች ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2018 (ኢዜአ)፦የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በአግባቡ በመጠቀም የለማች ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የአሁኑ ትውልድ ሃላፊነት መሆኑ ተገለጸ።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ዘንድሮ የሚካሄደውን የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።
የቢሮው ሃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ እንደገለጹት፤ በክልሉ በዘንድሮው ዓመት 6 ሺህ 386 ተፋሰሶች ላይ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በሚሆነው መሬት ላይ የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥብቃና እንክብካቤ ሥራ ይከናወናል።
"የአካባቢ ልማት፣ እንክብካቤና ጥበቃ ለሀገር ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ከነገ ጥር 5 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለ60 ተከታታይ ቀናት የሚከናወን መሆኑንም አመልክተዋል።
የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በአግባቡ በመጠቀም የለማች ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የአሁኑ ትውልድ ሃላፊነት እንደሆነ የገለጹት አቶ ጌቱ፤ ለልማት ስራው ስኬታማነት አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ እና የባለሙያ ስልጠና መከናወኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ በተከናወኑት የተፋሰስ ልማትና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ተከላ ስራዎች ክልሉ የነበረው የደን ሽፋን ማደጉን ገልጸዋል።
በዚህም ደርቀው የነበሩ ምንጮችና ኩሬዎች እንዲያገግሙ እና በበርካታ አካባቢዎች ላይ የአየር ንብረትና የመሬት ስነ ምህዳር እንዲሻሻል ማድረጉን ተናግረዋል።
በዚህም ቀድሞ ለእርሻ አመቺ ያልነበሩ መሬቶች ጭምር ለግብርና ሥራ እየዋሉ በመምጣታቸው በክልሉ ወጣቶችና አርሶ አደሮች ተደራጅተው በልዩ ልዩ የግብርና ስራዎች ላይ በመሰማራት ምርትና ምርታማነት ላይ ተጨባጭ ውጤት እየታየ መምጣቱን አመልክተዋል።
በበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት በተከናወነባቸው ቦታዎች ላይ በክረምቱ ወራት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ ገልጸው፤ ዘንድሮ በሚካሄደው የተፋሰስ ልማት ስራም የክልሉ ህዝብ በሙሉ አቅሙ በመሳተፍ ውጤታማ ስራ እንዲያከናውን አቶ ጌቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ ስራ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በነገው እለት የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በቡኖ በደሌ ዞን ይጀመራል።