የወል ትርክት መገንባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የወል ትርክት መገንባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2018 (ኢዜአ)፦የወል ትርክት መገንባት ለሀገረ መንግሥት ግንባታና ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት ወሳኝ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የጋራ ሀገራዊ ትርክቶችን ለመቅረጽ ያለመ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ በጅማ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ የወል ትርክት ያሉ ክፍተቶችን የሚያስታርቅ፣ በብዝኃነት ውስጥ ያሉ የአብሮነት እሴቶችን ለማጎልበት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የወል ትርክትን መገንባት ለሀገረ መንግሥት ግንባታና ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ከፋፋይ ትርክትና እሳቤዎችን ማስወገድ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በሕብረ ብሔራዊ አንድነት ወደ ከፍታ ጉዞ መጀመሯን በማንሳት፥ ትውልዱን በጋራ ትርክት መቅረፅ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት አስተሳሳሪ ትርክትን ለመገንባት በቅንጅት መሥራት አለባቸው ብለዋል።
ብሔራዊ መግባባትን ለማጎልበት አሁን ትክክለኛው ጊዜ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱን በአግባቡ በመጠቀምና ሀሳብን በሰለጠነ መንገድ በማቅረብ ለውጤታማነቱ መረባረብ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ታሪክን ለመማሪያነት ብቻ መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት አቶ መሐመድ፣ ከትናንት ጠቃሚ የሆኑ የታሪክ እሴቶችን በመውሰድ ዛሬም ተደምረን የላቀ ታሪክ መሥራት ይኖርብናል ብለዋል።
በኮንፈረንሱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፣ የመስኖና ቆላማ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባኤ ሰዓዳ አብዱረህማን፣ በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከፍያለው ተፈራ፣ ሌሎች የፌዴራልና የክልል አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።