ቀጥታ፡

በአቢጃታ ሐይቅ ላይ 600 ሜትር የሚረዝም የኤሌክትሪክ መስመር ተዘረጋ

አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2018 (ኢዜአ)፡- አምራች ኢንዱስትሪው ያጋጠመውን የኃይል መቆራረጥ ለመቅረፍ 600 ሜትር የሚረዝም የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በአቢጃታ ሐይቅ ላይ መከናወኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።


 

የመስመር ዝርጋታው የተከናወነው፤ ከአቢጃታ ሐይቅ ሶዳ አሽ እያወጣ ለብርጭቆ፣ ለጠርሙስ፣ ለጨርቃጨርቅ እንዲሁም ለንፅኅና መጠበቂያ አምራች ድርጅቶች ለሚያቀርበው አቢጃታ ሻላ አክሲዮን ማኅበር መሆኑም ተገልጿል።

አምራች ኢንዱስትሪው በአቢጃታ ሐይቅ ከመጠን ያለፈ የውኃ ሙሌት ምክንያት የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ወድቀው፣ የኃይል መቆጣጠሪያ ጣቢያውም በውኃ ተጥለቅልቆ የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ እንደነበር ተጠቁሟል።


 

ከአካባቢው ተፈጥሯዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ምሰሶ ሲቆም በንፋስ ሲወድቅና በመሬቱ ጨዋማነት ሲበላ አገልግሎቱም በተደጋጋሚ ጥገና ሲያከናውን በርካታ ጊዜያት ማለፋቸውን ተቋሙ ለኢዜአ የላከው መረጃ አመላክቷል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ምሰሶውን ከመሬት ይልቅ በውኃ ውስጥ በመትከል ኢንዱስትሪው ያልተቆራረጠ ኃይል እንዲያገኝና የምርት ሥራውን እንዲያከናውን ማስቻሉን አረጋግጧል።


 

በዚህም ኢንዱስትሪው የማይዋዥቅ የኃይል አቅርቦት እንዲያገኝ ተደርጎ ወደ ሥራ እንዲመለስ ከማድረግ ባሻገር በአካባቢው ለሚገኙ 150 አባወራዎች ኃይል እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም