ኢትዮጵያ ለስደተኞች እያደረገች ያለው ድጋፍ ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለስደተኞች እያደረገች ያለው ድጋፍ ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው
አዲስ አበባ፤ጥር 4 /2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍ በቀነሰበት በአሁኑ ወቅት ለስደተኞች እያደረገች ያለው ድጋፍ ያላትን ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚያመላክት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር አስታወቀ።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለስደተኞች የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር (ዩኤንኤችሲአር) የኢትዮጵያ ተወካይ አይሳቱ ንዳዬ፥ ኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን ስደተኞች እና ጥገኝነት ፈላጊዎችን ማስጠለሏን ጠቅሰው፥ በተጨማሪም ለተፈናቃይ ዜጎችም ድጋፍ እያደረገች እንደምትገኝ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
የስድተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ተቋማዊ አቅም ለብሄራዊ የስደተኞች ምላሽ ስርዓት ቁልፍ ምሰሶ መሆኑን አመልክተዋል።
አገልግሎቱ በስደተኞች ጥበቃ፣ ሰብዓዊ ድጋፍ እና ለተፈናቃይ ዜጎች የረጅም ጊዜ መፍትሄዎችን በማበጀት ቁልፍ ሚና እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
ከስደተኞች እና ተፈናቃዮች መካከል ሴቶች እና ህጻናት አብዛኛውን ድርሻ እንደሚይዙ ገልጸው፥ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፉን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር (ዩኤንኤችሲአር) ከኢትዮጵያ መንግስት፣ከክልል መንግስታት እና ከተቀባይ ማህበረሰቦች ጋር በስደተኞች ጉዳይ ውጤታማ እና የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት በትብብር እየሰራ ነው ያሉት።
ዩኤንኤችሲአር ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ስትራቴጂካዊ አጋርነት በመተማመን፣ በጋራ ኃላፊነት እና የጋራ ራዕይ ማዕከል ባደረገ መልኩ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ስድተኞችን በመጠበቅ፣መጠልያ በማዘጋጀት፣አስቸኳይ ድጋፎችን በማድረግ፣ ዘላቂ መፍትሄዎችን በመስጠት እና ማህበረሰቦች ለአደጋ የማይበገር አቅም እንዲኖራቸው እያከናወነች ያለውን ስራ አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ ግጭቶች በተበራከቱበት እና የሰብዓዊ እርዳታ እየቀነሰ በመጣበት ወቅት ለስደተኞች በሯን ከፍታ በማስተናገድ ያላትን ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና አመራር ሰጪነት ማሳየቷን ነው የገለጹት።
በኢትዮጵያ የዩኤንኤችሲአር ቢሮ መጠልያዎችን ማዘጋጀት እና ዜጎች ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
ብሄራዊ አቅምን ማጠናከር እና ስደተኞች በዘላቂነት ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩ ማድረግ ለስደተኞች እና ለተቀባይ ማህበረሰቦች የጋራ ጠቀሜታን በማስገኘት ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
ሁሉንም ስደተኞች እና ተፈናቃዮች አካታች ስራ ለማከናወን የተቀናጀ አሰራርን መከተል እንደሚገባ ነው ንዳዬ ያሳሰቡት።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር (ዩኤንኤችሲአር) እና የኢትዮጵያ መንግስት ከእ.አ.አ 1966 አንስቶ በስደተኞች እና ተፈናቃዮች ጉዳይ ላይ በትብብር እየሰሩ ይገኛሉ።