ማንችስተር ዩናይትድ ከኤፍኤ ካፕ ውድድር ተሰናበተ - ኢዜአ አማርኛ
ማንችስተር ዩናይትድ ከኤፍኤ ካፕ ውድድር ተሰናበተ
አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2018(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ኤፍኤ ካፕ የሶስተኛ ዙር መርሃ ግብር ብራይተን ማንችስተር ዩናይትድን 2 ለ 1 አሸንፏል።
ማምሻውን በኦልድትራፎርድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ብራጃን ግሩዳ እና ዳኒ ዌልቤክ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ቤንጃሚን ሼስኮ ለዩናይትድ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
የማንችስተር ዩናይትዱ ሼ ሌሲ በ89ኛው ደቂቃ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።
ለብራይተን አንድ ጎል ያስቆጠረው ብራጃን ግሩዳ የጨዋታ ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።
ውጤቱን ተከትሎ ብራይተን ወደ አራተኛ ዙር አልፏል።
የ13 ጊዜ የኤፍኤ ካፕ አሸናፊ ማንችስተር ዩናይትድ በሶስተኛ ዙር ከውድድሩ ተሰናብቷል።
ዛሬ በተደረገው ሌላኛው ጨዋታ አርሰናል ፖርትስማውዝን 4 ለ 1 አሸንፏል።
በፍራተን ፓርክ በተካሄደው ጨዋታ ጋብርኤል ማርቲኔሊ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሲሰራ የፖርትስማውዙ አንድሬ ዶዜል በራሱ ላይ ቀሪዋን ግብ ለአርሰናል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ኮልቢ ቢሾፕ ለፖርትስማውዝ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አስቆጥሯል።
14 ጊዜ ዋንጫ በማንሳት የውድድሩ ስኬታማ ክለብ የሆነው አርሰናል ወደ አራተኛ ዙር አልፏል።
ሶስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የኤፍኤ ካፕ የሶስተኛ ዙር መርሃ ግብር እስከ ጥር 5 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
የወቅቱ የኤፍኤ ካፕ አሸናፊ ክሪስታል ፓላስ ትናንት በማክስፊልድ 2 ለ 1 ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ ሆኗል።
155 ዓመታትን ያስቆጠረው ኤፍኤ ካፕ የዓለም አንጋፋው የክለቦች ውድድር ነው።