ቀጥታ፡

በኤል ክላሲኮ ደርቢ ባርሴሎና ሪያል ማድሪድን በማሸነፍ የስፔን አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን አነሳ

አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2018(ኢዜአ)፦ በስፔን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ባርሴሎና ሪያል ማድሪድን 3 ለ 2 አሸንፏል።

ማምሻውን በሳዑዲ አረቢያ ኪንግ አብዱላህ ስፖርትስ ሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ራፊኒያ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ሮበርት ሌዋንዶስኪ ቀሪዋን ጎል ለባርሴሎና ከመረብ አሳርፏል።

ቪኒሺየስ ጁኒየር እና ጎንዛሎ ጋርሺያ ለሪያል ማድሪድ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

በ91ኛው ደቂቃ የባርሴሎናው ፍራንኪ ዲ ዮንግ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

የባርሴሎናው ራፊኒያ በውድድር ዓመቱ በሁሉም ውድድሮች ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ 11 ከፍ አድርጓል።

በጨዋታው ባርሴሎና በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስድም ሁለቱም ቡድኖች በቁጥር ተቀራራቢ የግብ እድሎችን ፈጥረዋል።

ጨዋታው አዝናኝ እና ሳቢ ፉክክር ተደርጎበታል።

ውጤቱን ተከትሎ ባርሴሎና ለ16ኛ ጊዜ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን አንስቷል። የባለፈው ዓመት ክብሩንም ማስጠበቅ ችሏል።

ባርሴሎና ለበርካታ ጊዜ ውድድሩን በማሸነፍ ስኬታማ ክለብ ነው።

ሪያል ማድሪድ 13 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ይከተላል።

የስፔን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በስፔን ላሊጋ እና በስፔን ጥሎ ማለፍ ዋንጫ በተመሳሳይ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን የያዙ ክለቦች የሚሳተፉበት ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም