በአስተዳደሩ በምግብ ዋስትናና በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉ ወገኖች ኑሮ እንዲሻሻል የሚደረገው ድጋፍ ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በአስተዳደሩ በምግብ ዋስትናና በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉ ወገኖች ኑሮ እንዲሻሻል የሚደረገው ድጋፍ ይጠናከራል
አምቦ፤ጥር 3/2018 (ኢዜአ)፦የአምቦ ከተማ አስተዳደር በምግብ ዋስትናና በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉ ወገኖች ኑሮ ይበልጥ እንዲሻሻል ድጋፉ እንደሚጠናከር የአስተዳደሩ ከንቲባ ሃጫሉ ገመቹ ገለጹ።
በአምቦ ከተማ በሁለተኛ ዙር የምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍቲኔት የኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም በመሳተፍ ሽግግር ያደረጉ 1ሺህ 176 ተጠቃሚዎች ዛሬ ተመርቀዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርአቱ ላይ የተገኙት የአምቦ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃጫሉ ገመቹ፣ ከዚህ ቀደም የህብረተሰቡ የሥራ ባህል አለመጎልበት ጋር ተያይዞ ሰርቶ ለመለወጥና ልማትን ለማፋጠን ተጽዕኖ ሲያደርግ ቆይቷል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ህብረተሰቡ በልማት ሥራዎች በንቃት እንዲሳተፍ መደረጉ ተጠቃሚነቱን ከማሳደግ ባለፈ የሥራ ባህሉን እየቀየረው መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ሰርቶ በመለወጥ የራሱን ኑሮ ከመምራት ባለፈ በሃገራዊ እድገት ውስጥ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን አመልክተዋል።
በተለይም የልማታዊ ሴፍቲኔት የኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም ተግባራዊ ከሆነ በኋላ የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች የጊዜ አጠቃቀምና የቁጠባ ባህል ማደጉን ነው የጠቆሙት።
በከተማዋ የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተለያዩ ኢንሼቲቾች መተግበራቸውንም ከንቲባ ሃጫሉ ጠቅሰዋል።
ህብረተሰቡን ከተረጂነትና ጠባቂነት ለማላቀቅ የተጀመሩ ኢኖሼቲቮች እንደሚቀጥሉ ገልጸው፣ በተለይ በምግብ ዋስትናና በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉ ወገኖች ኑሮ ይበልጥ እንዲሻሻል አስተዳደሩ የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል ብለዋል።
የአምቦ ከተማ አስተዳደር የምግብ ዋስትና እና የልማታዊ ሴፍቲኔት የኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ድሪርሳ በበኩላቸው፣ ከተረጂነት ለመውጣት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በፕሮግራሙ ታቅፈው ውጤታማ በመሆን የተሸጋገሩና ዛሬ ለምረቃ የበቁ ወገኖች በከተማ ግብርና፣ በፅዳት፣ውበትና በተፋሰስ ልማት ስራዎች ተሰማርተው ሲሰሩ የቆዩ መሆናቸውን ገልጾዋል፡፡
በሁለተኛ ዙር የምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍቲኔት የኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም ተሳትፈው የተመረቁት ወገኖች ወደፊት ሥራቸውን በውጤታማነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ 77 ሚሊዮን 616 ሺህ ብር በድጋፍ መሰጠቱንም ተናግረዋል፡፡
ዜጎች በፕሮግራሙ መታቀፋቸው ሰርተው ለመለወጥ ከማስቻሉ ጎን ለጎን የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያሳድጉና በከተማዋ የልማት ሥራዎች ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በፕሮግራሙ ታቅፈው ውጤታማ ከሆኑት መካከል በከተማው የያእ ገዳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተረፈ ሙለታ በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከመታቀፋቸው በፊት በችግር ውስጥ ይኖሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
በፕሮግራሙ ከታቀፉ በኋላ የጀመሩት ሥራ ውጤታማ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ካፒታላቸውን በማሳደግ ወደ ከብት ማድለብ ሥራ መሸጋገራቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በባለሙያዎች የተለያዩ ስልጠናዎችን ማግኘታቸው በስራቸው ውጤታማ ለመሆን እንዳገዛቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላው ነዋሪ ወይዘሮ ብርቄ ባሊ ናቸው።
ሰርተው ከሚያገኙት ገቢ የቁጠባ ባህላቸው ማደጉንም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በተሰማሩበት የዶሮ እና የበግ እርባታ ሥራ ውጤት በማስመዝገብ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እያስተዳደሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።