የህዝቦችን አብሮነትና ወንድማማችነትን የሚያጎለብቱ እሴቶችን በጥናትና ምርምር ማልማትና መጠቀም ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የህዝቦችን አብሮነትና ወንድማማችነትን የሚያጎለብቱ እሴቶችን በጥናትና ምርምር ማልማትና መጠቀም ይገባል
ሲዝ፣ ጥር 3/2018 (ኢዜአ)፡- የህዝቦችን አብሮነትና ወንድማማችነትን የሚያጎለብቱ ባህላዊ እሴቶችን በጥናትና ምርምር ማልማትና መጠቀም እንደሚገባ የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን ገለጹ።
የቤንች ዘመን መለወጫ "ቢስት ባር"ን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ የፓናል ወይይት በዞኑ ሲዝ ከተማ ተካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን እንደገለጹት "ቢስት ባር" በቤንቾች መንደር የጋራ ደስታ የሚጎላበት እና የደረሰ አዝመራን ሰብስበው ፈጣሪን የሚያመሰግኑበት ባህላዊ ኩነት ነው፡፡
በዓሉ ዘመን ከመለወጥ ባሻገር የደረሰን እህል ከጎረቤት ጋር በአንድነት በመቅመስ የሚከበር መሆኑ የአብሮነትና የወንድማማችነት እሴቱ ጎልቶ የሚንጸባረቅበት እንደሆነም ገልጸዋል።
እነዚህ እሴቶች ለአካባቢውና ለሀገር ልማት መጎልበት ያላቸውን ፋይዳ በጥናትና ምርምር በማስደገፍ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሠራ አመልክተዋል።
የሼይ ቤንች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ክፍሌ ጎበዜ በበኩላቸው በዓሉ የያዛቸውን ቱባ ባህሎች ከአካባቢው መስህብ ስፍራዎች ጋር በማስተሳሰር የቱሪዝም ሀብት እንዲሆን ለማስቻል ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
ከአባቶቻችን የመጣውን አብሮ ሰርቶ አብሮ የማደግና የመተባበር ልምድ ወጣቱ አውቆት በመተግበር ለሀገር እድገት ሚናውን እንዲወጣ ማስቻል አለብን ሲሉም ገልጸዋል።
የ"ቢስት ባር" ፓናል ውይይት ላይ "ኢኮኖሚያዊ ሥርዓትና የቢስት ባር ባህላዊ መሠረቶች" በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረቡት ካሳሁን ሙላት(ዶ/ር) በዓሉ ከምርት ጋር የተገናኘ በዓል በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍ እንደሚል ተናግረዋል።
በተለይም ከ"ቢስት ባር" ማግስት ለቀጣዩ ዓመት ሰፊ የግብርና ሥራ ለማከናወን ቤንቾች ወደ ማሳቸው የሚዘምቱበት መሆኑ ዘላቂና አስተማማኝ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋገጥ ዕሴቱ ጉልህ እንደሆነ አብራርተዋል።
እነዚህን ባህላዊ ሥርዓቶች ከዘመናዊ እውቀት ጋር በማስተሳሰር የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።
የፓናል ውይይቱ ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማንን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በዓሉ ጥር 4 እና 5 ቀን 2018ዓ.ም በደማቅ ሥነ ሥርዓት በሼይ ቤንች ወረዳና ሚዛን አማን ከተማ ይከበራል።